ቀጥታ፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ላቀ ውጤታማነት አሸጋግሯል

አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018 (ኢዜአ)፦የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ወደ ላቀ ውጤታማነት ማሸጋገሩን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መለሠ መና ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የሀገሪቱን ቁልፍ የመንግሥትና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማትን ያሰባሰበው “የፋይናንስ እመርታ በኢትዮጵያ” ኮንፈረንስ መካሄዱ ይታወሳል።

በኮንፈረንሱም በኢትዮጵያ ኢንቨትመንት ሆልዲንግስ ስር የሚገኙ የልማት ድርጅቶች የነበረባቸውን የፋይናንስ፣ የኦዲት፣ የካፒታል፣ የብድር ጫና እና የኮርፖሬት አስተዳደር ችግር በመቅረፍ ዘመናዊ የባለቤትነት፣ የአስተዳደር ስርዓት እና ዓለም አቀፍ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓት እንደተዘረጋላቸው ተገልጿል።

ዘመናዊ የኦዲት ስርዓት እንዲከተሉ መደረጉን እና ይህም ካጋጠማቸው የኢኮኖሚ ስብራት ወጥተው በፍጥነት ውጤታማ እንዲሆኑ አስቸሏል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መለሠ መና ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከ40 በላይ የመንግስት ልማት ድርጅቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ድርጅቶቹን ከተሰጣቸው ተልዕኮና ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አንጻር የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመደገፍ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

በለውጡ መንግሥት የተደረገውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ተከትሎ የልማት ድርጅቶች ከነበሩበት ኪሳራ ወጥተው ወደ ትርፋማነት መሸጋገራቸውን  አንስተዋል።

የልማት ድርጅቶቹ ተኪ ምርት በማምረት ከውጭ የሚገባ ምርት መጠን እንዲቀንስ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ እና ለዜጎች የስራ እድል እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እያበረከቱ ነው ብለዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅትም ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት እና ለቀጣይ ትውልድ መሸጋገር የሚችል ሃብት በመፍጠርና በማፍራት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል በበኩላቸው፣ ከለውጡ በፊት አብዛኛዎቹ የልማት ድርጅቶች ዘመናዊ አሰራርን ባለመከተላቸው ለኪሳራ ተዳርገው መቆየታቸውን አስታውሰዋል። 

የለውጡ መንግስት የተከተለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ድርጅቶቹ ያለባቸውን ዕዳ በማቃለልና ከኪሳራ እንዲወጡ በማድረግ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጦችን አምጥቷል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ድርጅቶቹ የሃብት አማራጮችን በማስፋት በኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና ለመጫወት ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥር የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶች ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ውስጥ የ12 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን ከፍተኛ ታክስ ከፋዮች መሆናቸውን አንስተዋል። 

ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት ከ228 ቢሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ታክስ መክፈላቸውን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም