ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል፣ ምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ አስተዳደር ከ11ሺህ በላይ ከሆኑ የኢኮኖሚ ድርጅቶች መረጃ ይሰበሰባል

ሐረማያ ፤ጥር 14/2018 (ኢዜአ) ፡-በሐረሪ ክልል፣ ምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ አስተዳደር ከ11ሺህ በላይ ከሆኑ የኢኮኖሚ ድርጅቶች  መረጃ የመሰብሰብ ስራ ይከናወናል።

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሐረር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ለሚያከናውኑ የመስኩ ባለሙያዎች  ስልጠና እየሰጠ ነው።

በአገልግሎቱ የሐረር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሙክታር ጀማል እንደገለጹት ስልጠናው ከሐረሪ ክልል፣ ምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ 625 መረጃ ሰብሳቢዎች፣ ተቆጣጣሪዎች እና አስተባባሪዎች እየተሰጠ ነው።


 

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ለ10 ቀናት በሚሰጠው በዚሁ ስልጠና በሶስት የተለያዩ ክፍሎች ላይ ያተኮረ ሙያዊ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።  

በዚህም በሐረሪ ክልል፣ ምስራቅ ሐረርጌ ዞንና ማያ ከተማ አስተዳደር ከተመረጡ 11ሺህ 567 የኢኮኖሚ ድርጅቶች  የሰው ሃይላቸውን፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸውንና  ወጪና ገቢያቸውን ጨምሮ ሌሎችም መረጃዎች ይሰበሰባሉ ብለዋል።

እንደ አቶ ሙክታር ገለጻ ከጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም  ጀምሮ ወደ ዋናው  የመረጃ መሰብሰብ ስራ እንደሚገባም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዘርፈ ብዙና የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥናቶችን በማከናወን  መረጃዎችን በመሰብሰብ ይተነትናል ያሉት ደግሞ የስልጠናው ዋና አስተባባሪ አቶ እንዳሻው ፈለቀ ናቸው። 


 

ስልጠናው  የኢኮኖሚ ድርጅቶችን መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ግንዛቤን ለቆጣሪዎች በመስጠት ስራውን  ለማሳካት ያለመ ነው ብለዋል።

የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራም የአገራችንን የኢኮኖሚ ሃብት ደረጃ ለማወቅ እንዲሁም ድርጅቶች ያላቸውን የሰው ሃይልና ሌሎች መረጃዎቻቸውን ለመለየትና ለጥናትና ምርምር፣ ለፖሊሲ ዝግጅት በማዋል ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ብለዋል።


 

ስልጠናውን እየተከታተሉ ከሚገኙት መካከል ማዓዛ ሀብታሙ እንደገለጸችው ስልጠናው የጠራ መረጃ በመሰብሰብ  ለአገራዊ  እድገት መሰረት እንዲጣል የሚያግዝ ነው ብላለች።

ስልጠናው በኢኮኖሚው ዘርፍ የተመዘገበውን ስኬት ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ ነው ያለው ደግሞ ሌላው ሰልጣኝ ሸምሸዲን አብዶ ነው።


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም