ቀጥታ፡

የመንግስት የሰላም ጥረትና የህብረተሰቡ ትብብር በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት መፍጠር አስችሏል

ደሴ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ የመንግስት የሰላም ጥረትና የህብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት መፍጠር አስችሏል ሲሉ በደሴ ከተማ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ልማትን ለማሳለጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና መወጣታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።


 

መንግስት ለሰላም አማራጭ ሰፊ እድል በመስጠት ተደጋጋሚ ጥሪ በማድረግ የመጣውን ውጤት በተመለከተ ኢዜአ በደሴ ከተማ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን አነጋግሯል።

ካነጋገርናቸው መካከል ሸህ መሀመድ ሰይድ እና አቶ ይመር አሊ፤ መንግስት በታጋሽነት ለሰላም የሰጠው ሰፊ እድልና ተደጋጋሚ ጥሪ ያስመሰግነዋል ብለዋል።

የመንግስት የሰላም ጥረትና የህብረተሰቡ ጠንካራ ትብብር ታክሎበት በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና መረጋጋት መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።

በመንግስት የሰላም ጥሪ መሰረት ወደ ሰላማዊ ህይወት የተመለሱትን አመስግነው አሁንም በጥፋት ተግባር ላይ የሚገኙ ሁሉ እድሉን ሳያባክኑ ሰላምን እንዲመርጡ መልእክት አስተላልፈዋል።


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የሀገር ሽማግሌ አቶ እሸቱ ይማም፤ የክልሉ መንግስት ለሰላም የሰጠው እድልና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል የመጡ የቀድሞ ታጣቂዎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙና ሕብረተሰቡን በልማት እንዲክሱ እየተፈጠረ ያለው እድል የሚበረታታ ነው ብለዋል።

የቀሩትም መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ አባቶቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም