የኢትዮጵያ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል በማድረግ ምቹ የከተሜነት ምኅዳር የመፍጠር ጥረት ውጤታማ እየሆነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል በማድረግ ምቹ የከተሜነት ምኅዳር የመፍጠር ጥረት ውጤታማ እየሆነ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ የከተሜነት ምኅዳር የመፍጠር ጥረት ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እና ቢግ ዊን ፊላንትሮፒ የኢትዮጵያን ከተሞች የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ የመሠረተ ልማት ግንባታ ርዕይ የሚደግፍ የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።
በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ከተሞችን የትራንስፎርሜሽን ጉዞ የሚያሳልጥ የከተሞች ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይፋ ሆኗል።
በዚሁ ወቅት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፤ የኢትዮጵያ ከተሞች መስፋፋት በኢኮኖሚ ዕድገትና በሥራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ የሃብት ምንጭነት እያገለገሉ ነው ብለዋል።
የከተሜነት ምኀዳሩ ለነዋሪዎች ምቹ የማድረግ ጥረትም የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
አዲሱ የከተሞች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብርም የከተሞችን የመሠረተ ልማትና መሠረታዊ አገልግሎቶች በራስ የገቢ አቅም የሚደግፉበትን ሥርዓት እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የንብረት ታክስ አስተዳደር ሥርዓቱን በማዘመን የከተሞችን ገቢ የማመንጨት አቅም የሚያሻሽል ብሔራዊ የካዳስተር፣ የመሬት ሊዝና የንብረት ታክስ አሰራር መፈጠሩን አንስተዋል።
በብድር፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት አማካኝነት የግሉ ዘርፍ የከተሞችን የመሠረተ ልማት ግንባታ የሚደግፍበት የፋይናንስ አቅርቦት ሥርዓት መገንባቱንም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል በማድረግ ለነዋሪዎች ምቹ የከተሜነት ምኅዳር የመፍጠር ጥረት ፍሬ እያፈራ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ከተሞችን ለአፍሪካ ከተሞች አርዓያ የማድረግ ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ከተሞች የትራንስፎርሜሽን ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በስኬት ለመምራትም ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጋር በቅርበት የሚሰራ የቴክኒክ ቡድን እንደሚዋቀር አብራርተዋል።