ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በልማትና መልካም አስተዳደር ዘርፎች ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል

አሶሳ፤ ጥር 14/2018(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በልማትና መልካም አስተዳደር  ዘርፎች ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።


 

የክልሉ መንግስት የ2018 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸም ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት እየተገመገመ ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ ቃሲም ኢብራሂም የክልሉን መንግስት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት በዝርዝር አቅርበዋል።

በሪፖርታቸውም ባለፉት ስድስት ወራት በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን 5 ቢሊዮን 194 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡንና 4 ሺህ 158 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባቱን በተሻለ አፈጻጸም አንስተዋል።


 

ይህም በክልሉ እየተከናወኑ ላሉ ዘርፈ ብዙ የልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ እና ለሌሎችም የልማት ተግባራት ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር እንደሚያስችል አንስተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተደድር አሻድሊ ሀሰን፤ ባለፉት ስድስት ወራት ከክልሉ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ጋር የተመጣጠነ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ የኢንቨስትመንት አቅሞችን  በማልማት የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ  ተግባራት በሰፊው እየተተገበሩ መሆኑን አንስተው፤ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

በቴክኖሎጂ የታገዘ የአገልግሎት አሰጣጥን በማስፋት ዜጎች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ እና ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረት የሚያስችሉ ተግባራትም ተከናውነዋል ብለዋል።

በከተማ እና በገጠር  እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ልማት በላቀ የህዝብ ተሳትፎ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፥ በሌማት ትሩፋት እና ሌሎች የልማት ኢንሼቲቮችም ቀጣይነት ያለው ውጤት እየተመዘገበባቸው መሆኑን አንስተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑትን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ፍጥነትና ፈጠራ በታከለበት መንገድ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው የገለጹት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም