ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ በሀገራት መካከል ፍርደኞችን የማስተላለፍና የወንጀል ጉዳይ የአሳልፎ መስጠት አዋጆችን አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ሀገራት መካከል ፍርደኞችን የማስተላለፍ እና የወንጀል ጉዳይ የአሳልፎ መስጠት አዋጆችን አጽድቋል።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 9ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።


 

በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ፍርደኞችን የማስተላለፍ ስምምነት በኢትዮጵያና በሕዝባዊት ሪፐብሊክ ቻይና እንዲሁም በኢትዮጵያና በብራዚል ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን የአሳልፎ የመስጠት ስምምነቱ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እና በደቡብ አፍሪካ ሪፐብሊክ መንግሥታት መካከል እንደተደረገም ተመላክቷል።

በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት ከሀገራቱ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ፍርደኞችን የማስተላለፍና የወንጀል ጉዳይ የአሳልፎ የመስጠት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ በአብላጫ ደምጽ አጽድቋል።

አዋጆቹም ፍርደኞችን የማረም ሂደት የበለጠ ውጤታማ በማድረግ ኢትዮጵያ ከሀገራቱ ጋር ያላትን የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚያስችል ተገልጿል።  


 

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ መካከል የሕክምና መሳሪያ አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ-2 ማስፈፀሚያ የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ላይ መክሯል።

በኢትዮጵያ አቪዬሽን ሴኩዩሪቲ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ የፌዴራል የስፖርት ልማትና አስተዳደር እንዲሁም የሕብረት ሥራ ማሕበራት ላይ የቀረቡ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም