በከተማዋ የቱሪስት ፍሰትና የቆይታ ጊዜን የሚያሳድጉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የቱሪስት ፍሰትና የቆይታ ጊዜን የሚያሳድጉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ ነው
ባህር ዳር፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመርና የቆይታ ጊዜን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ገለጸ።
በባህር ዳር ከተማ ጣና ሃይቅ ለ9ኛ ዙር የታንኳ ቀዘፋ ውድድርና የጀልባ ትርኢት እየተካሄደ ይገኛል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው እንደገለጹት፤ "የጥርን በባህር ዳር" መርሃ ግብር ልዩ ልዩ ኹነቶች የከተማዋን የቱሪዝም እንቅስቃሴ እያሳደገው ይገኛል።
የዚሁ አካል የሆነው የጣና ላይ የታንኳ ቀዘፋ ውድድር እና የጀልባ ትርኢት የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት ለማሳደግና የቆይታ ጊዜን ለማራዘም ማገዙንም አክለዋል።
"ጥርን በባህር ዳር " አካል የሆነው በጣና ላይ የሚከናወነው የታንኳ ቀዘፋ ውድድር ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የቱሪስቱን ፍሰት በመጨመርና የዘርፉን አቅም ለማሳደግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን መደገፍ እንዲሁም የኮሪደር ልማት ማከናወኑን አንስተዋል።
የባህር ዳር ከተማን የቱሪስት ፍሰት በመጨመርና የዘርፉን አቅም ለማሳደግ መሰል ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ብርሃን ንጉሴ በበኩላቸው፤ የከተማዋን ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በፍጥነትና በጥራት በማከናወን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይም የኮሪደር ልማት ስራዎች የባህር ዳር ከተማን ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ምቹ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
"ጥርን በባህር ዳር" መርሃ ግብር አካል የሆነው የጣና ላይ የታንኳ ቀዘፋ ውድድር እና የጀልባ ትርኢት የከተማዋ የቱሪዝም ዘርፍ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲያድግ ማገዙን ጠቁመዋል።
ውድድሩን ይበልጥ በማስተዋወቅ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ለማድረግና የመንግስታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እንዲመዘገብ ሁላችንም የሚጠበቅብንን መስራት ይገባል ብለዋል።
በውድድር ስነ ስርዓቱ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።