ቀጥታ፡

በአማራ ክልል መንግሥት እና በአፋህድ መካከል የተደረሰው ስምምነት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው 

አዲስ አበባ፤ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ  ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት  መካከል የተደረሰው ስምምነት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ የሰላም  ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ ገለጹ።

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል የተደረገውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ማዕቀፍ ውጤታማ ለማድረግ የማስፈፀሚያ ስምምነት ተፈርሟል።


 

የአማራ ክልል የሰላምና ደህነት ቢሮ ሃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ወታደራዊ አስተዳደር መምሪያ ሃላፊ እያሱ አባተ (ረዳት ፕሮፌሰር )ስምምነቱን ፈርመዋል።

በስምምነቱ ዝርዝር ሂደቶች ፣የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ማቋቋምና ሌሎች ጉዳዮችም ተካተዋል።

ሃይልን በመጠቀም የሚመለስ ጥያቄ የለም ያሉት የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ፥ ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ወደ ሰላም ሊመጡ ይገባል ብለዋል።


 

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአፋህድ መካከል የተደረሰው የዘላቂ ሰላም ስምምነት ስቃይ እንዲያበቃ የሚያደርግ ትልቅ እርምጃ ነውም ብለዋል፡፡

ሌሎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችም ይሄን አርአያ ተከትለው ወደ ሰላም ሊመጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የዘላቂ ሰላም ስምምነቱ ማስፈጸሚያ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።


 

ስምምነቱ ለህዝብ ሰላም እፎይታን ከመስጠት ባለፈ የውጭ ጣልቃ ገቦችን ሴራ ለማክሸፍ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።

የአፋህድ ምክትል ሊቀ መንበርና ወታደራዊ አዛዥ ኮለኔል ፈንታው ሙሃባ በበኩላቸው፥ ወደ ስምምነቱ የመጣነው የአማራ ህዝብ ግጭትን ከዚህ በላይ መሸከም የማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው ብለዋል።


 

ከውጭ ሃይሎች ጋር በመተባበር የአገርን ጥቅም አሳልፈን ላለመስጠት በመወሰናችን ጭምር ነው ወደ ስምምነት የመጣነው ሲሉ ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም