ቀጥታ፡

በክልሉ የማህበረሰቡን ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች  ይጠናከራሉ

ሆሳዕና፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ የጤና መድህን አገልግሎት ሽፋንን በማሳደግ የማህበረሰቡን ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እና የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በተገኙበት ክልላዊ የማህበረሰብ ጤና መድህን የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንዳሉት፤ በጤና ልማት ዘርፍ እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል የጤና መድህን አገልግሎትን በሁሉም አካባቢዎች ለማህበረሰቡ በፍትሀዊነት ማዳረስ አንዱ ነው። 


 

ለዚህም ስኬት የጤና ፋይናንስ ስርዓትን በማሻሻልና የማህበረሰብ ጤና መድህን አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ በአነስተኛ ወጪ የማህበረሰቡን ጤና ለማስጠበቅ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት ከ859 ሺህ በላይ አባወራዎችንና እማወራዎችን የማህበረሰብ ጤና መድህን አባል በማድረግ ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የጤና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የሕክምና ግብዓት የማሟላት ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰሩ ሥራዎች ውጤት ቢመዘገብም የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከማሳደግና ከሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ውስንነት እንደነበር አስታውሰዋል።


 

በመሆኑም በ2017 በጀት ዓመት በትግበራ ምዕራፍ የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠልና ችግሮችን በመፍታት የማህበረሰቡን ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎች  ይጠናከራሉ ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ነው የገለጹት።

በመሆኑም አመራሩ የማህበረሰቡን ፍትሀዊ የጤና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ የክልል፣ የዞን፣ የልዩ ወረዳና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም