በሕገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ ከ133 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል - ኢዜአ አማርኛ
በሕገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ ከ133 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል
ደሴ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ ከ133 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የሚኒስቴሩ የ2018 ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የሴክተር ጉባኤ በደሴ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ተቋማቸው ባለፉት ስድስት ወራት ገበያ በማረጋጋት፣ ህገ ወጥ ንግድን በመቆጣጠርና የወጪ ንግድን ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ ቆይቷል።
ገበያን ለማረጋጋት የገበያ ማዕከላትን ለማስፋትና ደረጃቸውን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶችም ተጨባጭ ውጤት ማስገኘታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የኑሮ ውድነትንና የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ ዝቅ ማድረግ መቻሉ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ነው የገለጹት።
በበጀት ዓመቱ ሰድስት ወራት በሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በተሰማሩ ከ133 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ለአብነት በማንሳት።
በሀገሪቱ ጤናማ የንግድ ሥርዓት በመፍጠር ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የወጪ ንግዱን ለማሳለጥ በተደረገ ጥረትም ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በክልሉ ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠርና ገበያን ለማረጋጋት በተሰራው ስራ ውጤት መመዝገቡን አንስተዋል።
ሁለገብ ዘመናዊ የገበያ መሰረት ልማት በመገንባት ውጤታማ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ባዩሽ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ በክልሉ ገበያን በማረጋጋትና ጤናማ የንግድ ውድድር መፍጠር የሚያስችሉ አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ የፌዴራል፣ የክልልና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።