ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ሂደት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ሂደት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል
ሰመራ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመምከርና የጋራ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ሂደት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲል የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በ11 ክልሎች፣ ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ወገኖችን ጭምር በማነጋገርና አጀንዳዎችንና ጠቃሚ ግብአቶችን በማሰባሰብ ሂደት ስኬታማ ተግባራትን ማከናወኑ ይታወቃል።
የምክክሩን ሂደት አካታች፣ አሳታፊና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ለማካሄድ ከዝግጅት እስከ ምክክር ሂደት ውጤታማ ተግባራት ማከናወን ተችሏል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአፋር ህዝብ ፓርቲ (አህፓ) ዋና ፀሃፊ አደም ዓሊ፤ በምክክር ሂደቱ እስካሁን ተሳታፊዎችን በመለየትና አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በዚህ ሂደት ፓርቲያቸው አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ ከማቅረብም ባለፈ ለምክክሩ ሂደት መሳካት የድርሻውን በመወጣት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመምከር ልዩነቶችን በውይይት በመፍታትና የጋራ መግባባት በመፍጠር ለብሔራዊ ጥቅሞች በጋራ በመቆም ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ይገባል ብለዋል።
ፓርቲያቸው የምክክሩን አስፈላጊነት በጽኑ በማመን የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተው፥ በስኬት እስከሚጠናቀቅም የበኩሉን ስራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሀገራዊ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሁሉም ዜጎች ለኑሮ የምትመች ሀገር ለመገንባት ምክክሩ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ ይህንን ማሳካትም የዚህ ትውልድ አደራ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በምክክር ችግሮችን መፍታት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በሂደቱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ታዋቂ ሰዎችና መላው ኢትዮጵያዊያን የድርሻቸውን ሊያበረክቱ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።