ቀጥታ፡

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከዲጂታል ዓለም ጋር ለመተዋወቅ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ወላይታ ሶዶ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከዲጂታል ዓለም ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅና በዘርፉ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው  የወላይታ ሶዶ ከተማ ሰልጣኞች ተናገሩ።

መንግስት በመላው ኢትዮጵያ ለአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የኮደርስ ስልጠና ለመስጠት ግብ ጥሎ እየሰራ ነው።

በወላይታ ሶዶ ከተማም 18 ሺህ 400 ዜጎችን በኢትዮ ኮደርስ ለማሰልጠን  እየተሰራ ይገኛል።

የኮደርስ ስልጠና የወሰዱ የከተማዋ ነዋሪዎች ስልጠናው ከዲጂታል ዓለም ጋር ይበልጥ እንዲተዋወቁና የራሳቸውን ሥራ በመፍጠር ተጠቃሚ ለመሆን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ሰልጣኞች መካከል አቶ ደምሴ አሻ፤ በኮደርስ በተለያዩ ዘርፎች የወሰዷቸው ስልጠናዎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማሳደግ በዲጂታል ዓለም እኩል ለመንቀሳቀስ የሚያስችል  ክህሎት እንዳስጨበጧቸው ገልጸዋል።


 

በአሁኑ ወቅትም ባገኙት እውቀት የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተጨማሪም በተለያዩ ተቋማት ያሉ ሠራተኞችን በማሰልጠን ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ስልጠናው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለኝን እውቀት አሳድጎልኛል ያሉት ደግሞ  ሒሩት አርጃ ናቸው።


 

በኢትዮ ኮደርስ የፕሮግራሚንግ ስልጠና መውሰዳቸውንና በአሁኑ ወቅት በሰውሰራሽ አስተውሎት ስልጠናቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከስልጠናው ዲጂታል ዓለምን የሚመጥን እውቀት መቅሰማቸውን ተናግረዋል።

ስልጠናው የኮምፒውተርና የዲጂታል እውቀቴን በማሳደግ ከዓለም ጋር ይበልጥ የምቀራረብበትን ዕድል ሰጥቶኛል ያሉት ደግሞ አቶ ሙሉጌታ ዶላ ናቸው።


 

በስልጠናው ያገኙት እውቀት በዲጂታል ዓለም ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋቸው ተናግረው፣ ያገኙት እውቀት ከተቋማዊ አሰራር ጋር በማስተሳሰር ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንዳስቻላቸውም ገልጸዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሻለ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ መምሪያው ስልጠናውን ተደራሽ በማድረግ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተጀመረውን ሥራ ለማገዝ እየሰራ ነው።


 

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ከተጀመረ ወዲህ በከተማው ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች ስልጠናቸውን አጠናቅቀው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ገልጸው፣ ከነዚህ ውስጥ 3ሺህ 480 የሚሆኑት ባለፉት ስድስት ወራት ስልጠናውን የወሰዱ ናቸው ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ዕቅዱን ለማሳካትም የአንድ ጀንበር ምዝገባ ንቅናቄ በማካሄድና በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ዜጎችን ለማሰልጠን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

‎ስልጠናው  በዲጂታል ክህሎት የዳበረ ማህበረሰብ ለመፍጠርና የዲጂታል ዓለምን በፍጥነት የሚላመድ ትውልድ ለማፍራት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም