የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማፋጠን ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማፋጠን ያግዛል
ሮቤ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ በዘርፉ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማፋጠን አጋዥ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በሚካሄደው 2ኛው ዙር የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ ላይ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የቴክኒክ አስተባባሪ ለሊሳ በሾ፣ በስልጠናው መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፣ የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራ መካሄድ ውሳኔ ሰጪ አካላት ጥራት ያለውና መረጃን መሰረት ያደረገ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ያግዛል።
በቆጠራው በመላው አገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚካተቱ ሲሆን ቆጠራው በሁሉም ከተሞች ቤት ለቤት በመዞርና በገጠር ናሙና በመውሰድ ይከናወናል ብለዋል።
የኢኮኖሚ ድርጅቶቹ ቆጠራ በዘርፉ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠልና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማፋጠን እንዲሁም የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦችን ለማመንጨት ጉልህ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።
ለኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራው የሚሳተፉ ከኦሮሚያ ክልል ከባሌ፣ ምሥራቅ ባሌ፣ምዕራብ አርሲ፣ምሥራቅ ቦረና እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ሊበን ዞኖች የተወጣጡ 734 የዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠናው የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።
ቆጠራው በዘርፉ ለሚዘጋጁ እቅዶች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትክክለኛ ግብዓት ለማግኘት እንደሚያስችል ጠቅሰው፣ የስልጠናው ተሳታፊዎችም የአቅም ግንባታ ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የባሌ ጎባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሽመልስ አሰፋ በበኩላቸው፣ ስልጠናው መረጃ ሰብሳቢዎች ጥራትና ወቅቱን የጠበቀ ተዓማኒነት ያለው መረጃ መሰብሰብ የሚችሉበትን ክህሎት እንዲያገኙ ያግዛል ብለዋል።
የኢኮኖሚ ድርጅቶች ቆጠራው በመላው ኢትዮጵያ ከመስከረም 2018 ጀምሮ መካሄድ መጀመሩ ይታወቃል።