በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር መተግበሩ የተሻለ ገቢ እንዲሰበሰብ አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር መተግበሩ የተሻለ ገቢ እንዲሰበሰብ አስችሏል
ነገሌ ቦረና፤ ጥር 14/2018 (ኢዜአ)፡- የግብር ከፋዩ ግንዛቤ በማደጉና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራር በመተግበሩ የተሻለ ገቢ መሰብሰቡን የምሥራቅ ቦረና ዞን ገቢዎች ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
በጽሕፈት ቤቱ የዕቅድ፣ በጀት ክትትልና ግምገማ ባለሙያ መዓዛ አሊ እንዳሉት፤ ገቢ የመሰብሰብ ዐቅምን አሟጦ ለመጠቀም የግብር ከፋዩን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ በትኩረት ሲሠራ ቆይቷል።
የገቢ አሰባሰቡን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ መደረጉም የገቢ ዐቅምን ማሳደግ ማስቻሉን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ከ854 ሚሊየን 528 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ጠቅሰዋል።
አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ341 ሚሊየን 502 ሺህ ብር ብልጫ እንዳለውም ለኢዜአ ተናግረዋል።
በነገሌ ቦረና ከተማ በሆቴል ንግድ የተሰማሩት አመለወርቅ ክፍሌ እንዳሉት፤ ዐቅምን ያገናዘበ የግብር ውሳኔ መሰጠቱ ነጋዴው ግብሩን ያለቅሬታ እንዲከፍልና ዜጎች የተሟላ መንግሥታዊ አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል።
በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ሥራ የተሰማሩት ቢኒያም ተፈራ በበኩላቸው፤ ግብርን በወቅቱ በመክፈል ሕግና ሥርዓትን ማክበር እንዲሁም ፍትሐዊ የንግድ ውድድርን ማስፈን የነጋዴው ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የሀገር ልማትን ለማስቀጠል ግብር የመክፈል ግዴታ የተጣለበት ዜጋ ሁሉ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ያስረዱት ደግሞ ሌላኛዋ ግብር ከፋይ ብርቅነሽ ገብረሚካኤል ናቸው።
በታማኝነት ግብር በመክፈል ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ማስቆምና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉም አስተያየት ሰጭዎቹ በአጽንኦት ገልጸዋል።