በምርጫው በሐሳብ የበላይነት ለመወዳደር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምርጫው በሐሳብ የበላይነት ለመወዳደር የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው
ባሕር ዳር፤ ጥር 14/2018 (ኢዜአ)፡- በፓርቲዎች ዘንድ በምርጫው ለሕዝብ የሚበጁ ፕሮግራሞችን ይዞ በመቅረብ በሰለጠነ አግባብና በሐሳብ የበላይነት ለመወዳደር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።
የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀመንበር ተስፋሁን ዓለምነህ እንዳሉት፤ በምክር ቤቱ የታቀፉ ፓርቲዎች ለአባሎችና ደጋፊዎቻቸው ግንዛቤ በመፍጠር ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
የምርጫው ሂደት የሰለጠነ ፉክክር የሚካሄድበት፣ ተአማኒ፣ ፍትሐዊ፣ ነጻ፣ ግልጽና አካታች እንዲሆን የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
ለዚህም ፕሮግራም በመቅረጽ ለምርጫው ከመቅረብ ባለፈ ለአባላቸውና ለደጋፊዎቻቸው ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው የሚሠሩበትንና በፍትሐዊነት በሚዲያ ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ የሚያደርሱበትን ሁኔታ ከመፍጠር አንፃርም መንግሥት የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ፉክክር ከጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ እንቅስቃሴ በራቀ መልኩ በሰለጠነ አግባብና በሐሳብ የበላይነት በመወዳደር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሰረት ማኖር እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት የሚመሩበት የምርጫ ሥነ-ምግባር ደንብ በማዘጋጀት በምርጫው ለመሳተፍ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አመላክተዋል።
የሕዝብን ውሳኔ በማክበር የሚመጣውን ውጤት መቀበል የሁሉም ግዴታ መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።
7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በመጪው ግንቦት ወር እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።