ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ  ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ 

አዲስ አበባ፤ ጥር 14 /2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።  

ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል። 

ሲዳማ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች መካከል ስምንቱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ15ቱ ጨዋታዎች ላይ 20 ጎሎችን ሲያስቆጥር ስምንት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ቡድኑ በ30 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና 15 ጨዋታዎችን አከናውኖ በአምስቱ አሸንፎ በስድስቱ ተሸንፎ አራት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 

በጨዋታዎቹ ላይ 14 ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ጎሎችን አስተናግዷል። ኢትዮጵያ ቡና በ19 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። ኢትዮጵያ ቡና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል። 

በሌላኛው መርሃ ግብር መቻል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ። 

መቻል እስከ አሁን በሊጉ 15 ጨዋታዎችን አድርጎ ስድስት ጊዜ ሲያሸንፍ በአራቱ ተሸንፏል። በስድስቱ ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 20 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያስቆጥር 13 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ23 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባከናወናቸው 15 ጨዋታዎች በስድስቱ ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። አራት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 15 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 10 ግቦች ተቆጥረውበታል።

የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ22 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል። 

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ። 

ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ድሬዳዋ ከተማ በ18 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ መድን በ17 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ የ4 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል። መድን በበኩሉ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል።

ሁለቱ ቡድኖች ወደ ድል መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም