ቀጥታ፡

በአፋር ክልል 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለው "ፓራንትሮፐስ" የተሰኘ የሰው ዘር ቅሪተ አካል ተገኘ

አዲስ አበባ፤ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ አፋር ክልል ሚሌ-ሎጊያ ፓሊዮአንትሮፖሎጂ መካነ ቅርስ ስፍራ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለው "ፓራንትሮፐስ" የተሰኘ የሰው ዘር ቅሪተ አካል መገኘቱ ተገለጸ።

በአፋር ክልል ሚሌ-ሎጊያ የፓሊዮአንትሮፖሎጂ መካነ ቅርስ ስፍራ የተገኘው ቅሬተ አካሉም ከዚህ ቀደም ተገኝቶ የማያውቅ የቅድመ ሰው ዘር መሆኑ ተመላክቷል።

የቅድመ ሰው ዘር  ቅሪተ አካሉን ለማግኘት በአሜሪካ ቺካጎ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዘረሰናይ ዓለምሰገድ የተመራ ቡድን ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤሊያስ ሽኩር፤ የሀገር ውስጥና የውጭ ተመራማሪዎች የምርምር ውጤቶች የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበርካታ ቅድመ ሰው ዝርያ ቅሪተ አካል ግኝቶችም የዓለምን ማህበረሰብና ተመራማሪዎችን ቀልብ እየሳበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የፕሮፌሰር ዘረሰናይ ዓለምሰገድ የጥናት ቡድን በአፋር ክልል ያገኘው ፓራንትሮፐስ የተሰኘ የቅድመ ሰው ዘር ቅሪተ አካልም የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት ዳግም ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የቅድመ የሰው ዘር መገኛነት የጥናት ውጤት ማረጋገጫዎችም በቱሪዝም ዘርፍና በዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለቅድመ ሰው ዘር ቅሪት አካል ፍለጋና ለሰው ዘር አመጣጥ ጥናት ያላትን ልዩ ጠቀሜታ አጉልቶ እንደሚያሳይ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ወጣት ተመራማሪዎች በዘርፉ የሚኖራቸውን የላቀ የጥናትና ምርምር ሚና ለማሳደግም ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ለዚህም ብቃት ያላቸው የኢትዮጵያ አንትሮፖሎጂ ተመራማሪዎችን ለማፍራት ከውጭ የዘርፉ ሙያተኞች ጋር በቅርበት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የጥናት ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ዘረሰናይ ዓለምሰገድ በበኩላቸው፤ ፓራንትሮፐስ የቅድመ ሰው ዘር ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዓመታት በፊት የኖረ የነበረ የሰው ዝርያ መሆኑን የጥናት ውጤቶቹ እንደሚያሳዩ አረጋግጠዋል።

የቅድመ ሰው ዝርያው የተሻለ አካባቢን የመላመድ ባህሪ ያለው በመሆኑ በርካታ አካባቢዎች ላይ መኖሩን የሚያሳዩ የጥናት ውጤቶች እንደተገኙም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም