የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት በፍጥነት ሊጠናቀቅ ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት በፍጥነት ሊጠናቀቅ ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ የአዳማ-አዋሽ ምዕራፍ አንድ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ለሀገሪቱ ንግድ መሳለጥ ከፍተኛ ፋይዳ ስላለው በፍጥነት ሊጠናቀቅ እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ፣ መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ ላይ የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት 61 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ አለው።
ግንባታው በኢትዮጵያ መንግሥት እና በአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ እየተከናወነ እንደሚገኝ የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት በ40 ኪሎ ሜትር በሚጠጋው የመንገድ ክፍል ላይ የሁለተኛ ዙር አስፋልት ንጣፍ ሥራ መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም በአንድ ጊዜ አራት ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ብለዋል።
ግንባታው እንደ ወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ያሉ ተግዳሮቶች ገጥመውት የነበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተቋሙ አሁን ላይ እነዚህን በማለፍ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱን በፍጥነትና በጥራት ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ግንባታው ከተጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን መታዘባቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ችግሮችን በመቋቋም ለሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን የመንገድ ፕሮጀክት ሥራን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ለማፋጠን እየተከናወኑ ያሉ አበረታች ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መሐመድ አብዶ፤ የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ መጠናቀቅ የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ዘርፍ ለማሳደግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በመሆኑም አስተዳደሩ ግንባታውን በጥራትና በፍጥነት ሊያጠናቅቅ እንደሚገባ አሳስበው፤ ቋሚ ኮሚቴው ለሥራው ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት የሚጠበቅበትን ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የአዳማ-አዋሽ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የትራንስፖርት ኮሪደር አካል የሆነው የአዳማ-አዋሽ-መኢሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ኮሪደር ፕሮጀክት አካል መሆኑን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።