በክልሉ በበልግ አዝመራ የተሻለ ምርት ለማግኘት በተቀናጀ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በበልግ አዝመራ የተሻለ ምርት ለማግኘት በተቀናጀ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው
ቦንጋ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በበልግ አዝመራ የተሻለ ምርት ለማግኘት በተቀናጀ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የክልሉ ግብርና ቢሮ የ2018 የበልግና የተፋሰስ ልማት ስራዎች ዕቅድ ዙሪያ በቦንጋ ከተማ የንቅናቄ መድረክ አካሄዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ ባለፉት ጊዜያት በቅንጅት በተሰሩ የግብርና ልማት ስራዎች የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ በማስቀጠል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዘንድሮውን የበልግ አዝመራ እቅድ ለማሳካትም በንቅናቄ እንደሚሰራ ገልጸው፤ መሬት ኖሯቸው ማረስ የማይችሉ ሰዎች አቅም ካላቸው ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት።
በየደረጃው ያሉ የግብርና ባለሙያዎችም ግብዓት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ መሬትን በተገቢው ማረስና ሌሎች ምርታማነትን ማሳደግ የሚችሉ ዘዴዎችን በተገቢው በመተግበር እቅዱን ውጤታማ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረትና ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አርሶ አደሩም ራሱን ለመለወጥ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል የተፋሰስ ልማቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ባህል እየሆነ መምጣቱን ያነሱት ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፤ ዘንድሮም በተሻለ መልኩ ህብረተሰቡን በማነቃነቅ እንደሚሰራ አክለዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች የካፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳሻዉ ከበደ በዞኑ በበልግ አዝመራ ከ98 ሺህ ሄክታር መሬት በዋና ዋና ሰብልና በሆርቲካልቸር ለማልማት የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ለስኬቱም የግብዓት አቅርቦት፣ የእርሻ ትራክተሮች አቅርቦትና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በሰፊው በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ በተፋሰስ ልማት ላይም ህብረተሰቡን በሰፊው በማሳተፍ ርብርብ ይደረጋል ብለዋል።
የዳውሮ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ የእርሻ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ተካልኝ በቀለ የዘንድሮውን የተፋሰስና የበልግ ስራ በተለየ ትኩረት በመምራት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በተለይም የቴክኖሎጂና ግብዓት አጠቃቀም ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን በማረምና ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።