ቀጥታ፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተያዙ ግቦችን እውን ለማድረግ ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት ተሰጥቷል

ሀዋሳ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦የብልጽግና ፓርቲ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተያዙ ግቦችን እውን ለማድረግ የሰው ኃይል ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ለብልጽግና ፓርቲ ዋናና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች በተቀናጀ የተቋም ሀብት አስተዳደር ትግበራ ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል።


 

በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ሥራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል ሀገረፅዮን አበበ እንደገለጹት፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ በፓርቲው ለሰው ኃይል ግንባት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።


 

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ትግበራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት፣ ምቹ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋትና የሰው ኃይሉን በማብቃት ረገድ ውጤታማ ሥራ መሰራቱንም አስታውሰዋል።

በተጨማሪም አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማዘመን ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የተያዘው ግብ እንዲሳካም ፓርቲው ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተ መሆኑን ነው የገለጹት።

ሥልጠናው በየደረጃው ባሉ የፓርቲው መዋቅሮች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የስትራቴጂክ ሥራ አመራርና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ዋና ባለሙያ ጌትነት ሙላት በበኩላቸው፣ ስልጠናው በየደረጃው ያሉ የፓርቲው መዋቅሮች ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወጥ የአሰራር ሥርዓትን እንዲዘረጉ ያግዛል ብለዋል።


 

በየመዋቅሩ የሰው ኃይል፣ የግዥና ንብረት እንዲሁም የፋይናንስ አስተዳደርና ሌሎች ቁልፍ ተግባራትን በቴክኖሎጂ ታግዞ መስራት ዲጂታል ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ አንስተዋል።

ፓርቲው ለሰው ኃይልና ጠንካራ ተቋም ግንባታ የሰጠውን ትኩረት መሠረት በማድረግ በክልሉ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በፓርቲው የሲዳማ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ስትራቴጂክ ሥራ አመራርና ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ታምሩ ዩቴ ናቸው።


 

ሥልጠናው ተቋማትን በማዘመንና የሰው ኃይልን በማብቃት ወጥና ቀልጣፋ ዲጂታል ሥርዓት ለመገንባት ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለአራት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከፓርቲው ዋናና ከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡       

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም