አዲስ አበባን የትምህርትና የጤና ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርግ ምቹ ምኅዳር እየተፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን የትምህርትና የጤና ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርግ ምቹ ምኅዳር እየተፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2018 (ኢዜአ)፦አዲስ አበባን የትምህርትና የጤና ቱሪዝም ማዕከል የሚያደርግ ምቹ ምኅዳር እየተፈጠረ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን በዲጂታል ቴክኖሎጂና በሰው ሃይል ልማት የመዲናዋን የመስህብ መዳረሻነት ለማሳደግ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
የትብብር ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ የቱሪዝም ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ተፈራርመውታል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ መዲናዋን የቱሪዝም ስበት ማዕከል ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ ናቸው።
በቀጣይም የአዲስ አበባን ውበትና ገጽታ የገለጡ የልማት ሥራዎችን በዕውቀትና በዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት በማስደገፍ የቱሪዝም ተጠቃሚነትን ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በዚህም ከአራት ኪሎ እስከ አሜሪካ ኤምባሲ ድረስ በዩኒቨርሲቲ መንደርነት መሰየሙ ለትምህርት ቱሪዝም ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጨምሮ የጤና ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማዘመን የተሰሩ ሥራዎች ለመዲናዋ የጤና ቱሪዝም ዕድገት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አንስተል።
ይህም የአዲስ አበባን የትምህርትና የጤና ቱሪዝም ማዕከልነት አቅም የሚያጎለብት ምቹ ምኅዳር እየተፈጠረ ስለመሆኑ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው የአዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከልነት ለማስቀጠል በሚደረጉ ጥረቶች የሚጠበቅበትን ሙያዊ ኃላፊነት እንደሚወጣ አስታውቀዋል።
በስምምነቱ መሠረትም የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ምኅዳር ማዘመን የሚያስችል የሰው ሃብት ልማት፣ የጥናት ልየታና ዲጂታል ተደራሽነትን ለማስፋት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የተቋማቱ የትብብር ስምምነትም የባለድርሻ ተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር የዘርፉን እመርታዊ ስኬት ለማስቀጠል እንደሚረዳ ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የበርካታ ምሁራን መፍለቂያና ለሀገር ሁለንተናዊ ለውጥ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ የሚያበረክት አንጋፋ ተቋም ነው ብለዋል።
የተቋማቱ ስምምነትም በመዲናዋ የተመዘገቡ እመርታዊ የቱሪዝም ውጤቶችን በሰው ሃብትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ልማት እንዲሁም በጥናትና ምርምር ለማሳለጥ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።