ምርጫውን ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለማካሄድ በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫውን ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ለማካሄድ በሚደረገው ጥረት የድርሻችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል
ባህር ዳር ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ለማካሄድ በሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
በባህር ዳር ከተማ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት “ጤናማ ውድድር፣ ውጤታማ ትብብር፣ ገንቢ ምክክር ለሀገር ክብር” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ አካሂደዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በብልጽግና ፓርቲ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞላ ሁሴን፤ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል።
በመሆኑም ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ በሚደረገው ጥረት ፓርቲው የሚጠበቅበትን ግዴታና ሃላፊነት በብቃት ለመወጣት የተሟላ ዝግጅት ማድረጉን አረጋግጠዋል።
የፓርቲው አባላት በምርጫው ሂደት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ሥራ ከወዲሁ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።
የምርጫ ሂደት ዴሞክራሲያዊነት ማሳያ አጠቃላይ ሂደቱ መሆኑን ገልጸው በዚህ ጉዳይ ላይ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ተቀራርበው እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ተወካይ አቶ አለሙ ፈጠነ፤ የምርጫ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ በሚደረገው ጥረት ፓርቲው የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ጠቅላላ ምርጫው የህዝብ ድምጽና ውሳኔ ሰጭነትን በሚያከብር መልኩ እንዲካሄድና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እያደገ እንዲሄድ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል።
ከነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አቶ አሊ ሰኢድ፤ የዘንድሮውን ምርጫ ሰላማዊ ውድድር የሚካሄድበት እንዲሆን ከወዲሁ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ አባላት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።