አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል - ኢዜአ አማርኛ
አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3 ለ 2 አሸንፏል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቢኒያም አይተን እና አቡበከር ሳኒ በጨዋታ አህመድ ሁሴን በፍጹም ቅጣት ምት የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
አዲስ ግደይ እና ዩጋንዳዊው ሳይመን ፒተር የንግድ ባንክን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ከሶስት የሊጉ ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው አዳማ ከተማ በ26 ነጥብ ደረጃውን ከ7ኛ ወደ 4ኛ ከፍ አድርጓል። በውድድር ዓመቱ ስድስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
በአንጻሩ በሊጉ አምስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ17 ነጥብ ከነበረበት 13ኛ ደረጃ ወደ 14ኛ ዝቅ ብሏል። ቡድኑ ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አጥቂ አዲስ ግደይ በውድድር ዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት ወደ ስምንት ከፍ በማድረግ ተመሳሳይ የግብ መጠን ካለው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አቤል ያለው ጋር የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ መምራት ጀምሯል።