ቀጥታ፡

የወጣቶችን የፈጠራ አድማስ የሚያጎለብቱ የሥልጠና ዘርፎች እየተሰጡ ነው

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦የወጣቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትና የፈጠራ አድማስ የሚያጎለብቱ ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ የክህሎት ማበልጸጊያ የሥልጠና ፕሮግራሞች እየተተገበሩ መሆኑን የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ወጣቶች ችሎታቸውንና ሀሳባቸውን ትርጉም ወዳላቸው ፈጠራዎች መቀየር የሚያስችል "ክህሎት ኢትዮጵያ" የተሰኘ መርሃ ግብር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ሦስተኛውን ሀገር አቀፍ የክህሎት ውድድር ባስጀመረቡት ወቅት፤ የክህሎት ኢትዮጵያ እሳቤ ወጣቶች የማህበረሰቡን አንገብጋቢ ፍላጎቶች እንዲመረምሩና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ መፍትሔዎችን እንዲፈጥሩ የሚያስችል ነው ማለታቸው ይታወሳል።

የወጣት ፈጣሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የመጪው ዘመን የመወዳደሪያ መድረክ ነው፡፡

የዓለም ሁኔታ ሙያና ክህሎትን የሚያበረታታ ቢሆንም በኢትዮጵያ ለክህሎት ያለን ግንዛቤ ገና አላደገም ነው ያሉት።

ክህሎት የዘመናዊው ዓለም  የመወዳደሪያ መስክና ጸጋ መሆኑን ገልጸው፤ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና እንደ ሁለተኛ ምርጫ መታየት የለበትም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከለውጡ ወዲህ ያላትን  የወጣቶቿን እምቅ አቅም ታሳቢ ያደረገ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ መሪ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የክህሎት ትሩፋቶች መሆናቸውን በማንሳት፤ በኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የሥልጠናና የቅበላ አቅም እያደገ መምጣቱን አንስተዋል፡፡

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት የዘመኑ ኢንዱስትሪ የሚፈልጋቸውን ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት ነባር የሥልጠና ዘርፎችን እያሻሻለና አዳዲሶችን ገቢራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዚህም በ2018 ዓ.ም የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ሳይበር ደህንነት፣ ባዮ ሜዲካል ቴክኖሎጂ፣ ፕላስቲክ ቴክኖሎጂ፣ ሮቦቲክስ ቴክኖሎጂ እና ማንፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂን ጨምሮ 11 አዳዲስ የሥልጠና መስኮች ተጀምረዋል ብለዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ወደ ሥልጠና የሚገቡ ወጣቶችን ቁጥር ከማሳደጉም በላይ፤ አዳዲስ የሥልጠና ዘርፎችን ዘመኑን በዋጁ ቴክኖሎጂዎች አስደግፎ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህም ከንድፈ ሀሳብ የትምህርት አሰጣጥ ይበልጥ ለተግባር ሥልጠና ያተኮረ እንዲሆን አስችሎታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ በመደበኛና አጫጭር ሥልጠናዎች ስድስት ሚሊዮን ዜጎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሰልጣኞች ከሀገር ውስጥ ባሻገር ድንበር ተሻጋሪ አቅም እንደሚገነቡም ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ መንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የስልጠና ዘርፎች ሙያን በተግባር ማስተማር በሚችሉ ዘመኑ ባፈራቸው ግብዓቶች እንዲሟሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ወጣቶች መሰልጠን፥ ለሥራ መዘጋጀትና ችግርን የመፍታት አቅምን ማዳበር መሆኑን ተረድተው ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት እንዲገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም