ቀጥታ፡

የኮደርስ ስልጠና በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ነው

‎‎‎‎‎‎‎ዲላ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ የኮደርስ ስልጠና ጥልቅ እውቀት በማስጨበጥ በዘርፉ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ነው ሲሉ የኮደርስ ሰልጣኞች ተናገሩ።

በጌዴኦ ዞንና ዲላ ከተማ የስልጠናው ተሳታፊዎችና አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ባለሙያዎች፤የኮደርስ ስልጠና ጥልቅ እውቀት በማስጨበጥ በዘርፉ በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የስልጠና ዕድሉ ማንም ሊያመልጠው አይገባም ያሉት ሰልጣኞቹ፣ ስልጠናው ያላቸውን የቴክኖሎጂ እውቀት ከማሳደግ ባለፈ ስራቸውን በውጤታማነት ለማከናወን ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።  


 

በዞኑ የፋይናንስና ፕላን ልማት መምሪያ ባለሙያ አቶ ዳዊት ተፈራ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮ ኮደርስ በዳታ ፕሮግራሚንግ፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎትና በአንድሮይድ ዘርፎች የወሰዱት ስልጠና በዘርፉ የነበራቸውን ክህሎት እንዳሳደገው ተናግረዋል፡፡

በተለይ የዳታ ፕሮግራሚንግ ስልጠና ከተሰማሩበት የሥራ መስክ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ የመፈጸም አቅማቸውን እንዳሻሻለው ነው የገለጹት።


 

በአሁኑ ወቅትም በፕሮግራሚንግ ዘርፍ ተጨማሪ ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም እውቀታቸውን በማስፋት ተወዳዳሪነታቸውን እንደሚያሳድገው ተናግረዋል።

ከዲጂታል ዓለም ፈጣን እድገት ጋር አብሮ ለመጓዝ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መውሰድ ጠቀሜታ አለው ያሉት  የዞኑ ሥራና ክህሎት መምሪያ ባለሙያ አቶ ሰለሞን አበበ ናቸው።


 

ከዚህ ቀደም በዳታ ፕሮግራሚንግ ዘርፍ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸው በማይክሮ ሶፍት ሁሉም መተግበሪያዎች ላይ ያላቸውን ክህሎት አሳድጎላቸዋል።

በተለይ መረጃ አያያዛቸውን በማዘመን ምቹ የሥራ አካባቢ መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሰው በሌሎች ዘርፎችም አቅማቸውን ለማሳደግ የኮደርስ ስልጠና መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ስልጠናው ለቴክኖሎጂ ያለኝን ዝንባሌ ለማጎልበት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልኛል ያለችው ደግሞ የዲላ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12 ክፍል ተማሪ መድሀኒት ተገኝ ናት። 


 

የጌዴኦ ዞን ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ ሾንጣ እንዳሉት፤ በዞኑ ከ16 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠናውን ተከታትለው በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት አግኝተዋል፡፡

የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም በ80 ማዕከላት በዘመቻ እየተሰጠ ባለው ስልጠናም ከ22 ሺህ በላይ ዜጎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

‎በዲላ ከተማ እየተሰጠ ያለውን ስልጠና የመንግስት ሠራተኞችና አመራሮች፣ መምህራንና ተማሪዎች እየወሰዱ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዲላ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ፀሐይ ቦጋለ ናቸው። 

በዞኑና በዲላ ከተማ አስተዳደር በአንድ ጀንበር ንቅናቄ ከ34 ሺህ በላይ ዜጎች በ93 ማዕከላት የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እየወሰዱ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም