ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የመኖ እጥረትን ለመፍታት የጀመራቸውን የምርምር ሥራዎች የበለጠ ሊያጠናክር ይገባል

አዳማ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመኖ እጥረትን ለመፍታትና የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመራቸውን የምርምር ሥራዎች የበለጠ ሊያጠናክር እንደሚገባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት፣ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

የቋሚ ኮሚቴው አመራሮችና አባላት በአዳማ ከተማ በሚገኘው የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር ፕሮጀክቶች ላይ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።

በዚህ ጊዜ በምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱ የህብረተሰቡን ችግር በተጨባጭ መፍታት የሚችሉ ምርምሮች ለማከናወን እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።


 

ደረቅ ቆሻሻን ወደ እንስሳት መኖና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመለወጥ የሚያስችል የፈጠራ ቴክኖሎጂ እውን ማድረጉ የዚህ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ።

በገጠርም ይሁን በከተማ በዶሮና ዓሳ እርባታ የተሰማሩ ወጣቶችና አርሶ አደሮች መኖን በቀላሉ በቤታቸው እንዲያዘጋጁ ድጋፍ በማድረግ የመኖ እጥረትን ለመፍታት የኢንስቲትዩቱ ሚና ወሳኝ መሆኑንም ነው ያብራሩት።

ኢንስቲትዩቱ ጠቃሚ የምርምር ውጤቶችን በማስፋፋት በባዮ ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ሚናውን የበለጠ እንዲያጎላም ጠይቀዋል።

መኖን በአገር ውስጥ ማምረት የውጭ ምንዛሬን በማስቀረት የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢንስቲትዩቱ በዚህ ረገድ የጀመራቸውን የምርምር ሥራዎች የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።


 

የባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ፍሬው ታፈሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢንስቲትዩቱ ባለፉት ስምንት ወራት ቆሻሻን ወደ ከፍተኛ ፕሮቲን ያለው የእንስሳት መኖና የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚቀይር “ነብሳት” የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረፅ ውጤታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ፍራፍሬን ጨምሮ የግብርናና የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርቶችን በመፍጨትና በማብላላት  ወደ መኖና የተፈጥሮ ማዳበሪያ የሚቀይር መሆኑን አስረድተዋል። 


 

አሁን ላይ በሳምንት 10 ኩንታል የዶሮ መኖ በማምረት በአዳማ ሰርቶ ማሳያና የስልጠና ጣቢያ የዶሮ እርባታ መጀመሩን ገልጸዋል።

የዶሮ መኖን ከተረፈ ምርት የማግኘት፣ የማላመድና የማሳደግ ተግባራትን ወደ ተጠቃሚው ለማሸጋገር በሂደት ላይ መሆኑን አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም