ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ለ142 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ ተሰጥቷል

ጎንደር ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ በጎንደር ከተማ በ2018 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ከ43 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 142 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ መስጠቱን የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ገለጸ።

በጎንደር ከተማ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ባለሀብቶች፣ ዳያስፖራዎችና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም ተካሂዷል።


 

በዚሁ ጊዜ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ግርማይ ልጃለም፤ ፎረሙ ከተማዋ ያላትን የልማት ጸጋዎች ለማስተዋወቅና አዳዲስ ባለሃብቶችን ለመሳብ  ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በከተማዋ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ34 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 142 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።


 

ፈቃድ የተሰጣቸው ባለሃብቶች በአምራች ኢንዱስትር፣ በግብርናና በአገልግሎት ዘርፍ የሚሰማሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

እነዚህ ባለሃብቶች ወደ ሥራ ሲገቡ በከተማዋ ለሚገኙ 29 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለጽ።

እስካሁን ባለው ሂደት ለ17 ባለሃብቶች 17 ሄክታር የግንባታ ቦታ መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ወደ ግንባታ ለገቡ 22 አምራች ኢንዱስትሪዎች የመብራት፣ የውሃና የመንገድ መሰረተ ልማቶች መሟላቱን አመልክተዋል።

በከተማዋ የተከናወኑ የቱሪዝምና የኮሪደር ልማት ሥራዎች በርካታ ባለሀብቶች መዕዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ነው የመምሪያው ኃላፊ የተናገሩት።

በመምሪያው የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ፋሲል ዘውዱ ባቀረቡት የውይይት መነሻ፤ በከተማዋ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል ብለዋል።


 

በኢንዱስትሪ መንደር ውስጥ ከ700 ሄክታር በላይ ቦታ መዘጋጀቱን ለአብነት አንስተዋል።

የግንባታ ፍቃድ ወስደው ግንባታ ያልጀመሩና ቦታውን አጥረው በቆዩ ባለሃብቶች ላይ አስፈላጊው እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን አመልክተው፣7 ባለሃብቶች የወሰዱትን መሬት ባለማልማታቸው ወደ መሬት ባንክ ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።

የፎረሙ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ በከተማዋ እየታየ ያለው ሰላምና መረጋጋት ለኢንቨሰትመንት አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ሲሳይ ወንድሙና ዘይኑ መሀመድ ከተማዋ ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን አንስተዋል።

ከኢንቨስትመንት ፍቃድ አሰጣጥ ጀምሮ ያለው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የባለሀብቶችን ቀልብ የሚስብ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም