በወራቤ ከተማ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ የከተማዋን እድገት እያፋጠነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በወራቤ ከተማ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ የከተማዋን እድገት እያፋጠነ ነው
ወራቤ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ በወራቤ ከተማ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ግንባታው እየተከናወነ ያለው የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ የከተማዋን እድገት እያፋጠነ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሻፊ ሙዜ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በራስ አቅምና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በ1 ቢሊዮን 610 ሚሊዮን ብር 5 ነጥብ 73 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ እየተገነባ ነው።
ከከተማ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ ሥራ ጎን ለጎንም የፍሳሽ ማስወገጃ ትቦ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ነው።
በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ወደ ተግባር ከተገባው የመንገድ ስራም ውስጥ 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትሩ ለአስፓልት ንጣፍ ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል።
የአስፓልቱ ግንባታ ሥራ በከተማው በ1 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ የሚገኘውን የሶጃት ኢንዱስትሪ መንደርን ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎችን እንደሚያገናኝም ተናግረዋል።
የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሥራውን በታቀደለት ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
በከተማው የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ጅብሪል አማን ለኢዜአ እንዳሉት፤ በከተማ አስተዳደሩና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተሰራ ያለው የውስጥ ለውስጥ አስፓልት መንገድ ግንባታ ለከተማው የንግድ ሥራ መነቃቃት ከመፍጠር ባለፈ የትራንስፖርት ፍሰቱን እንደሚያቀላጥፈው ተናግረዋል፡፡
ለአስፓልት መንገዱ ሥራ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል፡፡
ሌላው የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ሸረፈዲን ሹሜ እንደገለጹት፤ ለአንድ አካባቢ ፈጣን እድገት መረጋገጥ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነትን ማስፋት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።
የከተማው አስተዳደር እያከናወነ ያለው ተግባር በከተማዋ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የከተማዋን ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡