ቀጥታ፡

የንግድ ስርዓቱን ለማዘመንና የግብይት ማዕከላትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል

ኮምቦልቻ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ ገበያውን ለማረጋጋት የንግድ ስርዓቱን ለማዘመንና የግብይት ማዕከላትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኮምቦልቻ ከተማ በ120 ሚሊየን ብር የተገነባው የገበያ ማዕከል ተመርቋል።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በተበታተነ መንገድ የሚደረግ ግብይትን በማሰባሰብና የግብይት ስርዓቱን በማዘመን የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እየተሰራ ነው።

በተጨማሪም የግብይት ስፍራዎችን ማልማት፣ ይዞታቸውን ማስከበር እንዲሁም ደረጃቸውን በማሻሻል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በከተሞች የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ተቋቁመው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እና በቅናሽ እንዲቀርብ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ የተመረቀው የገበያ ማዕከልም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው ስራው በሌሎች ከተሞችም መስፋት እንዳለበት ጠቁመዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ(ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የክልሉን ሰላም ከማጽናት በተጓዳኝ ለሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በተለይ ገበያን በማረጋጋት የኑሮ ውድነቱን ማቃለል እንዲቻል የገበያ ማዕከላትን የማስፋፋት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሀመድ(ዶ/ር) ቀደም ሲል ሸማችና አምራቹን የሚያገናኙ የገበያ ማዕከላት በስፋት ባለመኖራቸው የንግድ ስርዓቱ ለህገ ወጥ ተግባራት የተጋለጠ ነበር ብለዋል።

ይህን ችግር ለመቅረፍም በተለያዩ አካባቢዎች የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመው በቅርቡ ወደ ሥራ የገባው የደሴ ገበያ ማዕከልም ውጤታማ ሆኖ መቀጠሉን አንስተዋል።

ዘንድሮም ክልሉ ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ መድቦ የገበያ ማዕከላትን ለማስፋፋትና ደረጃቸውን ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መሀመድአሚን የሱፉ በበኩላቸው፣ በማዕከሉ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች ለሕብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርባሉ ነው ያሉት።

በምርቃቱ የፌዴራል፣ ከክልሎች የተውጣጡ የንግዱ ዘርፍ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም