የተፋሰስ ልማት የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሰረት ሆኗል- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
የተፋሰስ ልማት የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሰረት ሆኗል- ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ
ሀዋሳ፣ጥር 13/2018 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል የተፋሰስ ልማት ሥራ የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሰረት መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልል አቀፉን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ሀዌላ ወረዳ ዱለቻ ጠዌራኮ ቀበሌ አስጀምረዋል።
አቶ ደስታ ሌዳሞ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል።
የተፋሰስ ልማት ሥራው የተጎዳ መሬት እንዲያገግም በማድረግ የአፈር ለምነትን ከመጠበቅ ባሻገር ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ለገቢ ምንጭ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በጎርፍ ምክንያት የአፈር መሸርሸር ሲከሰት እንደነበር አስታውሰው፣ በተፋሰስ ልማት ሥራው በለሙ አካባቢዎች የእንስሳት መኖን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በተፋሰስ ልማት ሥራው የተገኙ ውጤታማ ሥራዎችን በማስቀጠል አረንጓዴና ለኑሮ ምቹ ስነምህዳር የመፍጠር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፋኖሴ መኮንን በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት እንደሃገር በተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 33 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚጠጋ መሬት መልማቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የአፈር ለምነትን በመጠበቅ የግብርና ምርታማነትን የማሳደግ፣ የውሃ አማራጮችን የማስፋትና በለሙ ተፋሰሶች የስራ ዕድል በመፍጠር ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በሲዳማ ክልል በ2018 በተለዩ 678 ንኡስ ተፋሰሶች የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን ከ147 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ ናቸው።
ለአንድ ወር በሚቆየው የተፋስስ ልማት ሥራ ተዳፋታማ በሆነ አካባቢዎች ለሚከናወን የጠረጴዛማ እርከን ስራና በእርሻ ማሳ ውስጥ ያለውን ባህር ዛፍ በመንቀል በትኩረት እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች የአፈር መከላትን መቀነስ፣ የውሃ አማራጮችን የማስፋትና ምርት የማይሰጡ አካባቢዎችን ወደ ምርት በማስገባት ዓመታዊ የሰብል መሬት ሽፋን ለማሳደግ መሰራቱን ገልጸዋል።
በቀበሌው ከዚህ ቀደም በለማ ተፋሰስ የሥራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት እንድሪያስ ኢዩኤልና ሰለሞን ዳንኤል በተፋስስ ልማት በለሙ አካባቢዎች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው በለማ ተፋሰስ ላይ ለአምስት ተደራጅተው በመንግስት በተመቻቸላቸው የገንዘብ ብድር በንብ በማነብ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በመርሃግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል አፈ ጉባኤ ፋንታዬ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ሃላፊዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ከፍሎች ተሳትፈዋል፡፡
በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይሳተፋል ተብሏል።