በሸገር ከተማ አስተዳደር በበጋ መስኖ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ አስተዳደር በበጋ መስኖ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ዘር ተሸፍኗል
ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ በሸገር ከተማ አስተዳደር በበጋ መስኖ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ በስንዴ ዘር መሸፈኑን የከተማው ግብርና ፅሕፈት ቤት ገለጸ።
በሸገር ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ ደረጀ በቀለ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በከተማ አስተዳደሩ በበጋ መስኖ እየተከናወነ ያለው የስንዴ ልማት ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፣ ግብርናውን የሚያዘመኑ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2018 ምርት ዘመን በከተማ አስተዳደሩ ባሉ 12 ክፍለ ከተሞች የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በመስኖ ስንዴ ልማቱ አርሶ አደሩ ተጨባጭ ውጤት እያገኘ በመሆኑ የሥራ ተነሳሽነቱ መጨመሩንም አመልክተዋል።
በዘንድሮ ምርት ዘመን ከ41 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ ስንዴ በዘር መሸፈኑንና ሰብሉ የፀረ አረም ኬሚካሎች ርጭትን ጨምሮ እየተደረገ ባለው እንክብካቤ ቡቃያው የተሻለ ቁመና ላይ መገኘቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አቶ ደረጀ በቀለ አስታውቀዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በማህበራት በኩል የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በወቅቱ ከማቅረብ ጎን ለጎን አርሶ አደሩ የመሬት ለምነትን ለመጨመር የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሰፊው አዘጋጅተው እንዲጠቀሙ መደረጉን ጠቁመዋል።
እንዲሁም በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠና መሰጠቱንና ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል።