የጉባ ብስራቶች ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩ ትልቅ ተስፋ ሰንቀናል - ኢዜአ አማርኛ
የጉባ ብስራቶች ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩ ትልቅ ተስፋ ሰንቀናል
አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ የጉባ ብስራቶች ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩ ተስፋ መሰነቃቸውን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መርቀው ስራ ባስጀመሩበት ወቅት በቀጣይ የሚገነቡ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ጉባ ላይ ማብሰራቸው ይታወቃል።
ይፋ የተደረጉት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን የሚያስችሉ ናቸው፡፡
የጉባ ብስራት ፕሮጀክቶች የኒውክሌር ማበልጸጊያ፣ የጋዝ ፋብሪካ፣ የነዳጅ ማጣሪያ፣ በአፍሪካ ግዙፉ አየር ማረፊያ፣ 2ኛውን የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ ማስጀመር፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች በመላው ሀገሪቱ ማስጀመር መሆናቸው ይታወቃል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በጉባ የተበሰሩት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ስብራት በማውጣት ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ከሰጡት መካከል አቶ ዳግማዊ ገነነ እንደተናገሩት፤ እነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለኢትዮጵያ ዕድገትና ከፍታ ግንባር ቀደም ፕሮጀክቶች እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ሀገር በግብርናው ዘርፍ የጀመረቻቸውን ውጤታማ ስራዎች ይበልጥ እንድታጎለብት የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ያለው ነው ብለዋል፡፡
የኒውክሌር ግንባታና ሌሎች ፕሮጀክቶችም ሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያያዘችውን ጉዞ ከግብ እንደሚያደርስ እምነታቸውን ገልፀዋል።
ፕሮጀክቶቹ በሀገር ዕድገት ላይ ከሚኖራቸው ከፍተኛ ድርሻ አኳያ ለተፈጻሚነታቸው በእውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በሁሉም ዘርፍ ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ አምሳሰው አበራ በበኩላቸው፤ የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካም ኩራት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ በአቪየሽን ዘርፍ ያላትን ግንባር ቀደም ተዋናይነት የሚያስቀጥል ብሎም የሀገርን ከፍታ የሚያረጋግጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መምህር ታደሰ መንግስቱ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቶቹ የይቻላል መንፈስን በተግባር የሚያረጋግጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለበርካታ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል በመፍጠር የዜጎችን የኑሮ ደረጃ እንደሚያሻሽሉም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ከጉባ ብስራቶች መካከል የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ እንደሚያጎላውና ለኢኮኖሚ ግንባታው ትልቅ አቅም እንደሚሆን የጠቆሙት ደግሞ አቶ አየለ አባቡላ ናቸው፡፡