ቀጥታ፡

የጤና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የጨው ምርቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ በህብረተሰቡ ላይ የጤና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የጨው ምርቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ ባከናወነው የተቀናጀ ክትትል በመጋዘን የተከማቹ ህገወጥ የጨው ምርቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ነጋሽ ስሜ እንደተናገሩት ባለሥልጣኑ ደህንነቱና ጥራቱ የተረጋገጠ ምርት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በትኩረት እየሰራ ነው።

በዚህም ሙሉ በሙሉና በከፊል የተቀነባበሩ ምርቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።

ባለሥልጣኑ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባደረገው ጥብቅና የተቀናጀ ቁጥጥር በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ በሚገኙ አፋር፣ አፊዴር ወለላ እና በሩዋቅ በተሰኙ ሦስት የጨው ምርቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል።

በዚህም ከ13 ሺህ ኩንታል በላይ ደረጃውን ያልጠበቀ የጨው ምርት በቁጥጥር ሥር መዋሉን ገልፀዋል።

ምርቶቹ የተቀመጠውን ብሔራዊ የአዮዲን ይዘት መስፈርት ሳያሟሉ የተመረቱ እንዲሁም ጨው ለምግብነት ከመቅረቡ በፊት መከናወን ያለበት የማጠብና የማጽዳት ሂደት ሳይደረግላቸው ለገበያ የቀረቡ መሆናቸውን አንስተዋል።

ምርቶቹ ለሰው ልጅ ጤና ጎጂ የሆኑ ባዕድ ነገሮችን ሊይዙ የሚችሉ መሆናቸውንም ነው ጨምረው የተናገሩት።

ባለሥልጣኑ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት መሰል የክትትል ስራዎችን በሌሎች የምርት ዘርፎች ላይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

ሕብረተሰቡም ጥራታቸው የተረጋገጡ ምርቶችን ብቻ በመጠቀም ለጤናው ጥንቃቄ እንዲያደርግ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም