ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ከልል ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በተከናወኑት ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል

አዳማ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከተረጂነት ለመውጣት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን የክልሉ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አብዱልአዚዝ ዳውድ (ዶ/ር) ገለፁ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የክልሉ መንግስት የስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዘንድሮው መኸር እርሻ 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በክላስተር የለማ መሆኑን ተናግረዋል።

ከልማቱም በዋና ዋና ሰብሎች የተሻለ አፈፃፀምና ምርት መገኘቱን ጠቅሰው የሜከናይዜሽን አገልግሎትና ተደራሽነት አበረታች ውጤት የተገኘበት ነው ብለዋል።

ለአብነትም በመኸር ከለማው መሬት 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሄክታር በኮምባይነር የታጨደ መሆኑን አንስተዋል።

በተያዘው በጋ ወራትም የታቀደውን ያህል መሬት ለማልማት ከ16 ሺህ 500 በላይ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ለአርሶ አደሩ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በእስካሁኑ ሂደትም ከ3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ በዘር መሸፈኑን ገልጸው በእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ረገድም 794 ሺህ ጥጆች በሰው ሰራሽ ስነ ዘዴ መወለዳቸውን አስረድተዋል።

በኢንሼቲቭ ተይዘው እየተተገበሩ ካሉ የግብርና ልማት ስራዎች መካከል የሻይ ቅጠል፣ የፍራፍሬና የቡና ልማት እና ችግኝ ዝግጅት በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ በግማሽ ዓመቱ የተሰሩ ስራዎች ምርታማነትን ለመጨመር የተያዘውን ግብ የሚያፈጥኑ ናቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል በገጠርና በከተማ የመሬት ካዳስተር ስርዓት ተግባራዊ የማድረግ ስራ አበረታች ውጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቅሰው በተለይም የመሬት ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓትን ከማዘመን አኳያ ተስፋ ሰጪ ስራዎች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

በክልሉ ከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና ዲጂታል ለማድረግ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተደራሽነት እንዲሁም በገጠር የተደራጁ የቀበሌ አስተዳደር መዋቅሮችም እየተጠናከሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የኑሮ ውድነትና የምርቶች ዋጋ ንረትን ለመቀነስ የሰንበት ገበያ ከማስፋት ባለፈ በምርት አቅርቦትና ሸማቹን ቀጥታ ከአምራቹ ጋር የማገናኘት ስራ አሁንም ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አመልክተዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም