ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ የምርጫ አዋጁን በማሻሻል በቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽና ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሄድ አስቻይ ሁኔታዎችን ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ አዋጁን በማሻሻል፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ግልጽ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ ማከናወን የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ማድረጉን የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 7 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲከናወንና ድምፅ መስጫውም ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲሆን መወሰኑ ይታወሳል።

ቦርዱ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ከግብዓት ማሟላት እስከ ሥልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች የተለያዩ ዝግጅቶችን ማድረጉን አስታውቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሀገሪቱ ምርጫና ድምጸ-ውሳኔ የሚያካሂድ ገለልተኛ ሕገ-መንግሥታዊ ተቋም ነው።

ቦርዱ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በቂ ዝግጅት ማድረጉን በሪፖርቱ ማረጋገጡን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ 7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊ የሕግ ማሻሻያዎች ማድረጉን ጠቁመዋል።

በተለይም አዋጅ ቁጥር 1162/2011ን በማሻሻል የዕጩዎችና የመራጮች ምዝገባ እንዲሁም ሌሎች የቦርዱ ሥራዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል።

የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ምርጫውን በመታዘብና ለመራጮች ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል።

መንግሥት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ መሠረት የምርጫውን ግልጽነትና ተዓማኒነት የሚያሳልጡ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የ7ኛው ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሂደት በብሔራዊ መግባባት እንዲከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቀሰው ለምርጫው ስኬታማነት ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም