ቀጥታ፡

ሀገራዊ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት የጋራ መፍትሄ ለማምጣት የሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍተኛ ነው -- አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌ እና ሀደ ሲንቄ

ሮቤ ፤ ጥር 13/2018(ኤዜአ)፡- ሀገራዊ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት የጋራ መፍትሄ ለማምጣት የሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የባሌ ዞን አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌ እና ሃደ ሲንቄ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ እየተንከባለሉ የመጡ ሀገራዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አካታችና ሰፋፊ ህዝባዊ ምክክሮችን በማካሄድ መግባባትን ለመፍጠር እየሰራ ነው፡፡

በሂደቱም እስካሁን ኮሚሽኑ ምክክር ማድረግ በሚቻልባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራዎችን በማገባደድ ላይ ይገኛል።

ጉዳዩን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የባሌ ዞን አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሃደ ሲንቄዎች ሀገራዊ ምክክሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲያሳትፍ መቆየቱን መታዘባቸውን ተናግረዋል።

የጋሠራ ወረዳ አባገዳ መሐመድ አሎ እንዳሉት የምክክር መድረኩ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመገንዘብ በሂደቱ በንቃት ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በእስከ አሁኑ ሂደትም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ባሳተፈ መልኩ ለሀገር ይጠቅማሉ የተባሉ ሀሳቦች መሰብሰቡ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ሀገራዊ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት የጋራ መፍትሄ ለማምጣት የሀገራዊ ምክክሩ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የአጋርፋ ወረዳ ሃደ ሲንቄ መኮ ሐጅ አደም ተመሳሳይ ሀሳብ በመጋራት የሀገራዊ ምክክሩ መሳካት በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት የጋራ መፍትሄ ለማበጀት ይረዳል ሲሉ ገልጸዋል።

የወረዳቸውን ህብረተሰብ በመወከል  በአዳማ ከተማ በምክክር ሂደቱ የተሳተፉ ሲሆን በመድረኮቹ ለአገር አንድነት የሚጠቅሙ ሀሳቦችን መስጠታቸውን አስረድተዋል።

በአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ በመሳተፍ ለሀገር ይበጃል ያሉትን የመፍትሔ ሃሳብ በነፃነት ማቅረባቸውና ሂደቱም ግልጽና አሳታፊ እንደነበረ የገለጹት ደግሞ የጎሮ ወረዳ የሀገር ሽማግሌው ሼህ ቡሽራ ሼህ ኡስማን ናቸው።

ሀገራዊ ምክክሩ መግባባት እና መቀራረብን  በማጠናከር ወደ ፊት የተሻለች ሀገር ለመገንባት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ለምክክሩ ስኬታማነት ድጋፋችን ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም