በአማራ ክልል የገበያ ማዕከላትን በማስፋት አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የማገናኘት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የገበያ ማዕከላትን በማስፋት አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የማገናኘት ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው
ኮምቦልቻ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የገበያ ማዕከላትን በማስፋት አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የማገናኘት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በኮምቦልቻ ከተማ በ120 ሚሊዮን ብር የተገነባው ሁለገብ ዘመናዊ የገበያ ማዕከል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢብራሂም መሀመድ (ዶ/ር)፤ ክልሉ የገበያ ማዕከላትን በማስፋት አምራችና ሸማቹን በቀጥታ የማገናኘት ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች እስካሁን ስምንት የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።
የገበያ ማዕከላትን ተደራሽነት በማስፋት አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑን አንስተው ማእከላቱ ህገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላሎችን ከግብይት ስርአቱ በማስወጣት አምራችና ሸማቹ በቀጥታ እንዲገናኙ የሚያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተማ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሀመድ (ዶ/ር) እና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።