የተፈጥሮ ፀጋን የማልማትና የመጠበቅ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ፀጋን የማልማትና የመጠበቅ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ካራት፤ ጥር 13/2018 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተፈጥሮ ፀጋን በማልማትና በመጠበቅ ለትውልድ ምቹ ሥነ ምህዳር ለማውረስ የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከር የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ክልል አቀፍ የ2018 በጀት ዓመት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና የበልግ አዝመራ ንቅናቄ መርሃ ግብር ዛሬ በኮንሶ ዞን በይፋ ተጀምሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉን የተፈጥሮ ፀጋ በማልማት ለትውልዱ ምቹ ስነ ምህዳር ለማውረስ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው።
ባለፉት ዓመታት በቅንጅት በተሰሩ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራዎችም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የተራቆቱ ተራራዎችን በማልማት ከስጋት ወደ ሀብት ምንጭነት ለመለወጥ መቻሉን ተናግረዋል።
በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ሥራም የኮንሶዎችን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ባህልን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋፋት ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በማልማትና በመጠበቅ ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ለትውልዱ ምቹ ሥነ ምህዳር ለማውረስ የተጀመረው ሥራ በቀጣይም ይጠናከራል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት በ159 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
በዚህም 1ሺህ 384 የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በተፋሰስ የለሙ አካባቢዎችን በስነአካላዊና ስነ ህይወታዊ ሥራዎች ፍራፍሬና የእንስሳት መኖ በማልማት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት ይሰራል ሲሉም አመልክተዋል።
እንደኃላፊው ገለጻ በክልሉ ባለፉት ስድስት ዓመታት የተፋሰስ ልማት ሥራ በተከናወነባቸው አካባቢዎች ከ164 ሺህ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል።
የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ በበኩላቸው በዞኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት እያሳደገው መምጣቱን ነው የተናገሩት።
ኮንሶዎች ከ500 ዓመታት በፊት የጀመሩት የእርከን ሥራ ለምርትና ምርታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዞኑ የተፈጥሮ ሀብቶችን በማልማት፣ በመንከባከብና በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ባህልን በማሳደግ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የበኩላችንን እየተወጣን እንገኛለን ያሉት ደግሞ የኮንሶ ዞን አርሶ አደር ካፖሌ ገድሻ ናቸው።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለአንድ ወር በሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተፋሰስ ልማትና የበልግ አዝመራ ንቅናቄ መርሃ ግብር ላይ የክልሉና የዞን ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የኮንሶ ዞን ነዋሪዎችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።