ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለፋይናንስ ተቋማት የደንበኞች አገልግሎትን ለማፋጠንና ደህንነቱን ለማስጠበቅ ትልቅ እገዛ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ለፋይናንስ ተቋማት የደንበኞች አገልግሎትን ለማፋጠንና ደህንነቱን ለማስጠበቅ ትልቅ እገዛ ያደርጋል
ጭሮ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፡- ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞችን መረጃ አያያዝ ለማዘመን፣ ፈጣንና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተገለጸ።
ኢዜአ በጭሮ ከተማ ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች ጋር በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ አገልግሎት ላይ ቆይታ አድርጓል።
የስራ ሀላፊዎቹ እንዳሉት ዲጂታል መታወቂያው የደንበኞች የዓይን፣ የፊት ገፅታና አሻራ በኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ በመያዝ አንድ ሰው ወጥ መረጃን ለመያዝ ከማጭበርበር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ነው።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጭሮ ኦዳ ቡልቱም ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ በላይ የሗላሸት እንዳሉት የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በሐሰተኛ መታወቂያ የሚፈጸሙ የማጭበርበር ተግባራትን ለመከላከል ያስችላል።
የዲጂታል መታወቂያ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ መረጃ መያዙ ተገልጋዩ አንድ ማንነት እንዲኖረው በማድረጉ ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባንኩ አዲስ ለጀመረው የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጠን የማሻሻል ስራን የሚያቀላጥፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአዋሽ ባንክ የጭሮ ቅርንጫፍ የደንበኞች አገልግሎት እና ኦፕሬሽን ስራ አስከያጅ አቶ ቴዎድሮስ ሰለሞን በበኩላቸው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ደንበኞችንና ባንኮች በተሟላ መልኩ እንዲተዋወቁ በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጡን የሚያቀላጥፍ ነው።
ደንበኛው በአንድ የፋይዳ ቁጥር ብቻ በመመዝገቡ ባንኮች የብድር አገልግሎት ሲሰጡ ደንበኞቻቸውን በሚገባ እንዲያውቁና የብድር ክትትሉን በተገቢው መልኩ እንዲያከናውኑ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ እየተተገበረ ያለውን ከወረቀት ነፃ አገልግሎት ለማቀላጠፍ የሚያግዝ ነውም ብለዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም የጭሮ ማዕከል ሽያጭ ባለሙያ አቶ ተንኮሉ በቀለ በበኩላቸው የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የአንድ ሰው መረጃን ወጥነት ባለው መንገድ በመመዝገብ ፈጣንና ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ የሚያሰፍን መሆኑን ጠቁመዋል።