ቀጥታ፡

አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊጉ ጥሎ ማለፍ የገባ የመጀመሪያ ቡድን ሆኗል

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተጠባቂ መርሐ-ግብር አርሰናል ኢንተር ሚላንን 3 ለ 1 አሸንፏል።

ማምሻውን በሳንሲሮ ስታዲየም በተካሄደ ጨዋታ ጋብርኤል ጄሱስ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ተቀይሮ የገባው ቪክቶር ዮኬሬስ ቀሪዋን ጎል ከመረብ አሳርፏል።

ፔታር ሱቺች ለኢንተር ሚላን ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል በ21 ነጥብ አንድ ጨዋታ እየቀረው ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለ የመጀመሪያ ቡድን ሆኗል።

አርሰናል በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ሁሉንም ጨዋታዎች ያሸነፈ ብቸኛው ክለብ ነው።

በውድድሩ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢንተር ሚላን በ12 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃን ይዟል።

በሌሎች መርሐ-ግብሮች የ15 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሪያል ማድሪድ ሞናኮን በሜዳው 6 ለ 1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል።

ኪሊያን ምባፔ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ፍራንኮ ማስታንቱኖ፣ ቪኒሺየስ ጁኒየር፣ ጁድ ቤሊንግሃም እና የሞናኮው ቲሎ ኬህረር በራሱ ላይ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

ጆርዳን ቴዜ ለሞናኮ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ውጤቱን ተከትሎ ሪያል ማድሪድ በ15 ነጥብ ሶስተኛ፣ ሞናኮ በዘጠኝ ነጥብ 20ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ስፖርቲንግ ሊዝበን የወቅቱን የዋንጫ ባለቤት ፒኤስጂን ሳይጠበቅ 2 ለ 1 አሸንፏል።

ሉዊስ ሱዋሬዝ ለስፖርቲንግ ሊዝበን ሁለቱን ግቦች ሲያስቆጥር ክቪቻ ክቫርትስኬሊያ ለፒኤስጂ ብቸኛውን ጎል ከመረብ አሳርፏል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስ ቦሩሲያ ዶርትሙንድን 2 ለ 0 ሲረታ ክርስቲያን ሮሜሮ እና ዶምኒክ ሶላንኬ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

የቦሩሲያ ዶርትሙንዱ ዳንኤል ስቬንሰን በ24ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ኮፐንሃገን እና ናፖሊ አንድ አቻ ተለያይተዋል። ጆርዳን ላርሰን ለኮፐንሃገን፣ ስኮት ማክቶሚናይ ለናፖሊ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

የኮፐንሃገኑ ቶማስ ዴላኒ በ35ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ኦሎምፒያኮስ ባየር ሌቨርኩሰንን 2 ለ 0 ሲረታ አያክስ ቪያሪያልን 2 ለ 1 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም