ቀጥታ፡

መቀሌ 70 እንደርታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አገኘ

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ16ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር መቀሌ 70 እንደርታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2 ለ 1 አሸንፏል። 

ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጊት ጋትኩት እና ፍፁም አለሙ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ሀብታሙ ሸዋለም ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

በውድድር ዓመቱ ሶስተኛ ድሉን ያስመዘገበው መቀሌ 70 እንደርታ በ16 ነጥብ ደረጃውን ከ18ኛ ወደ 16ኛ ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። 

በአንጻሩ በሊጉ ሶስተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። 

ዛሬ ቀን ላይ በተደረገ የ16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከነማ ከሀዲያ ሆሳዕና ዛሬ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በበዓሉ ምክንያት ያልተካሄደ ሲሆን በቀጣይ በሚገለጽ ጊዜ በተስተካካይ መርሃ ግብር እንደሚደረግ የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም