ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን ቦርድ አዲስ የአካባቢ ልማት ጥናት /LDP/ አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን ቦርድ የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግና ግዙፍ አለም እና አህጉር አቀፍ ኩነቶችን ማስተናገድ የሚያስችል አዲስ የአካባቢ ልማት ጥናት/LDP/ ተወያይቶ አጽድቋል።

በቦርዱ የፀደቀው ጥናት ሶስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንዳሉት የከንቲባ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል። እነዚህም ፦


 

የመንገድ ትስስርን ማስፋት እና ማዘመን ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም የመንገድ ኔትወርኮችን ማስፋፋት፣ ሰፋፊ የእግረኛና የሳይክል መንገዶችን መገንባት እንዲሁም ዘመናዊ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችንና ተርሚናሎችን ያካትታል።

ለታላላቅ ስፖርታዊ ኩነቶች የሚደረግ ዝግጅት፦ የአፍሪካ ዋንጫንም በብቃት ማስተናገድ እንድትችል በዝግጅት ላይ ትገኛለች። በተለይም በአደይ አበባ ስታዲየም ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች የዚሁ ዕቅድ አካል ናቸው።

በአጠቃላይ በFIFA ስታንዳርድ መሠረት የሚከተሉት መሰረተ ልማቶች እንደሚለሙም በመረጃው ተመላክቷል። እነርሱም፦

• የመንገድ እና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት፤

• የሆቴል፣ ሬስቶራንት እና ፔንሲዮን፣ በርከት ያሉ የተለያዩ የንግድ ቤቶችን የማስፋፋት ልማት፤

• የውኃ፣ የፍሳሽ፣ የቴሌኮም እና የኤሌክትሪክ ኃይል እና ሌሎች የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት፤

• የወንዝ ዳርቻ ልማት⁠፤

• ከስታድዮሙ ፊት ለፊት በከፊል እየለማ ባለው ዊንዶስ ኦፍ አፍሪካ ላይ የአረንጓዴ ፕላዛ፣ የጎልፍ ሜዳ፣ የአዳራሾች፣ የካፍቴሪዎች፣ የስፖርት ሜዳዎች፣ የተለያዩ መዝናኛዎች እና መሰል ልማቶች ይሰራሉ።

•የአሰራር ሂደቱ ነባርና አዳዲስ መሠረተ ልማቶችን አስተሳስሮ በስታድየሙ ዙሪያ ነባር መሰረተ ልማቶችን ባሉበት ማደስን ቅድያ በመስጠት፣ አዳዲሶቹን ደግሞ በነዋሪው፣ በመንግሥት፣ በባለሀብቱ እና በተቋማት ቅንጅት የሚለማ ይሆናል።

የትግበራ ሂደቱም ነዋሪውን በስፋት በማወያየት በፀደቀው ፕላን መሰረት ነዋሪውን እያገዝን ራሱ እንዲያለማው ማድረግ ቅድሚያና ትኩረት ይሰጠዋል።

ይህ እድል ለከተማዋ ነዋሪዎች ሰፊ የስራ እድል እና የኢኮኖሚ መነቃቃት የሚፈጥር በመሆኑ በትብብር እና በጋራ ለማሳካት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጥሪ ማቅረባቸውም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም