ቀጥታ፡

መተግበሪያው አገልግሎትን ለማቀላጠፍና ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፋ ያደረገው መተግበሪያ ዳያስፖራው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።

‎የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 'CBE Connect Digital Wallet' የተሰኘ ከውጭ ሀገር ገንዘብ ለመላክ የሚያስችል አዲስ መተግበሪያ ስራ አስጀምሯል። 


 

‎‎የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍጹም አረጋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባንኩ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በስኬት መሻገሩን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለሚደረገው ጉዞ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

‎ዛሬ ይፋ የተደረገው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዲያስፖራው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ከማስቻሉም ባለፈ፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከልና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፤ ባንኩ በየወቅቱ አሰራሩን በማዘመን ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


 

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ባንኩ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

ስራ ላይ የዋለው መተግበሪያ የባንኩን የዲጂታል ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑን ጠቅሰው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ደንበኞችን ይበልጥ የሚያስተሳስርና የሐዋላ ሂደትን የሚያቀላጥፍ መሆኑን ተናግረዋል።

መተግበሪያው በኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ባለው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን   መተግበሪያውን ከንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ያበለጸገው የስታር ፔይ  ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሱፍቃድ ጌታቸው  ገልጸዋል።


 

‎‎መንግስት ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የፈጠረው ምቹ ሁኔታ መሰል ፈጠራዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማበልጸግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም