የአምስት ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና የዲጂታል ክህሎት እንድናጎለብት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል - ኢዜአ አማርኛ
የአምስት ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና የዲጂታል ክህሎት እንድናጎለብት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦ የአምስት ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ሥልጠና ከዘመኑ ጋር አብረን መራመድ የሚያስችለንን የዲጂታል ክህሎት እንድናጎለብት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮልናል ሲሉ በመዲናዋ የኮደርስ ሰልጣኞች ገለጹ።
ወጣቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎታቸውንና እውቀታቸውን እንዲያዳብሩ መንግስት የአምስት ሚሊየን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር ዘርግቶ ብዙዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ኢዜአ ስልጠናውን በመውሰድ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣቶችንና የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበርን አነጋግሯል።
ማህበሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ወጣቶች የዲጂታል እውቀታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችል ስልጠና እንዲወስዱ እያገዘ እንደሚገኝም አስታውቋል።
ወጣት ደረጄ ማሞ ማህበሩ የአምስት ሚሊየን ኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የምንወስድበትን ምቹ ሁኔታን ፈጥሮልናል ብሏል፡፡
በማህበሩ እገዛ የዲጂታል ክህሎቱን ለማሳደግ የሚያግዘውን የኮደርስ ስልጠና በመውሰድ ራሱን ለማሻሻል መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
በዚህም ከኮደርስ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ የሆነውን ዌብ ፕሮግራሚንግ በመምረጥ ስልጠና እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ህይወት ገብረእግዚአብሄር በበኩሏ ከኢትዮ ኮደርስ የስልጠና አይነቶች አንዱ የሆነውን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መውሰዷን ገልጻለች።
ስልጠናው የዲጂታል ክህሎቷን ለማሳደገ አቅም እየፈጠራላት መሆኑንና ይህንንም በእለት ከእለት የስራ እንቅስቃሴዋ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግራለች።
በርካታ ሀገራትና ግለሰቦች በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ ስራዎቻቸውን እያከናወኑ መሆኑን የገለጸው ፋሲል ጉልላት እሱም ራሱን በቴክኖሎጂ ለማብቃት የአንድሮይድ የኮደርስ ስልጠና እየወሰደ መሆኑን ተናግሯል።
ወጣቶች ያለንን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትና እውቀት ለማዳበር እንደ ሀገር የሚፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ልንጠቀም ይገባል ብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት በረከት ቢርቢርሳ በበኩሉ፤ ወጣቶች የስራ እድል ፈጣሪና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የኮደርስ ስልጠና ሚናው የጎላ እንደሆነ ተናግሯል።
ማህበሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ወጣቶች ስለ ኮደርስ ስልጠና ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረጉን ጠቅሶ፤ አሁን ላይ 81ሺህ ወጣቶች የኮደርስ ስልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ጠቁሟል።