የተፋሰስ ልማት ሥራ ለምርታማነት መጨመር ከፍተኛ እገዛ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የተፋሰስ ልማት ሥራ ለምርታማነት መጨመር ከፍተኛ እገዛ አድርጓል
መቱ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፡- የተፋሰስ ልማት ሥራ ለምርታማነት መጨመርና ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን የቡኖ በደሌና የኢሉባቦር ዞኖች አርሶ አደሮች ተናገሩ።
በቡኖ በደሌ ዞን የዳቦ ሐና ወረዳ ነዋሪዎች አርሶ አደር ዲንቃ ገቢ እና ታሪኩ አብዲሳ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ እገዛ አድርጓል።
በተጨማሪም እየተመናመኑ የነበሩ የደንና የውኃ ሀብቶች እንዲመለሱ ማድረጉን ተናግረዋል።
የተፋሰስ ልማት ሥራ የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙና ምርታማነታቸው እንዲጨምር ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ በኢሉአባቦር ዞን የሁሩሙ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደሮች ተካልኝ ታደገ እና ዓለማየሁ በቀለ ናቸው።
የተፋስ ልማት የተከናወነባቸው አካባቢዎችን ከሰውና ከእንስሳት ንኪኪ በመጠበቅ ለመኖ ልማት ብሎም ለንብ ማነብ ሥራ እያዋሏቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ከተከናወነ የተፋሰስ ልማት የተገኘውን ተጠቃሚነት በመገንዘብ፤ በቀጣይም ሥራውን በባለቤትነት አጠናክረው ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የቡኖ በደሌ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አማን ደኑ በበኩላቸው፤ የተፋሰስ ልማት ሥራ በአርሶ አደሩ ዘንድ መደበኛ ተግባር ሆኖ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የዓየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል፣ ምርታማነትን ለማሳደግና የተፈጥሮ ሀብትን ለመጠበቅ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ወሳኝ ነው ያሉት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቻላቸው አዱኛ ናቸው።
ለሁለት ወራት የሚቆይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በዞኖቹ በ479 ተፋሰሶች ላይ እየተከናወነ ይገኛል።