በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቤቶችን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ቤቶችን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ትኩረት ተደርጓል
ጥር 12/2018 (ኢዜአ) - በኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቤቶች ያላቸውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ትኩረት መደረጉን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለጹ።
የህብረተሰቡን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተተገበሩ ካሉ ስራዎች መካከል ሊለሙ የሚችሉ መሬቶች ጾም እንዳያድሩ ሰብልን በብዛትና በስፋት ማልማት ነው።
በዚሁ ማዕቀፍ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ትምህርት ቤቶች በአጥር ግቢያቸው ያለውን መሬት በማልማት የትምህርት ቤት የተማሪዎች ምገባ መርሃግብርን በራሳቸው መሸፈን እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል።
የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ እንደተናገሩት፤ በክልሉ ከለውጡ ወዲህ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ በተሰራው ስራ ውጤት እየተገኘ ነው።
በተለይም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በመሸጋገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስትም ትውልድን በትምህርት እና በቴክኖሎጂ መገንባትን የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤቶችን ገቢ ማሻሻል እና የተማሪዎች ምገባ መርሃ-ግብርን የማጠናከር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በቂ የላቦራቶሪ እና የቤተ-መጻህፍት ግብዓቶችን ማሟላት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ለትምህርት ቤቶች በማቅረብ የዲጂታል ትምህርት አሰጣጥን በማጠናከር ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
እንደ አቶ አወሉ ገለጻ ከመንግስት፣ ከህዝብ እና ከለጋሽ አካላት የሚገኘው ገቢ ብቻውን ለትምህርት ጥራት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላትና ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል ትውልድ ለመፍጠር በቂ አይደለም።
በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሰፊ መሬት ቢኖራቸውም እስካሁን በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳያውሉ መቆየታቸውን ጠቅሰው ሰፊ መሬት ያላቸው ትምህርት ቤቶች መሬቱን በማልማት ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በበርካታ ትምህርት ቤቶች ስራው የተጀመረ ሲሆን በሰሜን ሸዋ ዞን ቅምብቢት ወረዳ የሚገኘው የሶምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለዚህ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቱ በክልሉ ቡሳ ጎኖፋ አማካኝነት ካለው መሬት ውስጥ በ12 ነጥብ 5 ሄክታር ላይ ስንዴ በማልማት 600 ኩንታል ገደማ ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ትምህርት ቤቱ በመንግስት ኢንሼቲቭ በመታገዝ የዶሮ እርባታ እና የወተት ላሞችን ማርባት፣ የበሬ ማድለብ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በዚህም ለተማሪዎች ምገባ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በራሱ በማሟላት ራስን የመቻል ደረጃ ላይ መድረሱን ጠቅሰው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የዚህ የትምህርት ቤት ተሞክሮ በዞኑ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች እንዲሰፋ ይደረጋል ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲን ጨምሮ የሰሜን ሸዋ ዞን ሀላፊዎች ቅምብቢት ወረዳ የሚገኘውን የሶምቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የልማት ሥራንም ጎብኝተዋል።