ቀጥታ፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከ47 ሚሊየን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን ተቻለ

ቦንጋ፤ ጥር 12/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት 47 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ከምዝበራ ማዳንና በኦዲት ግኝት ማስመለስ ተቻለ።

የክልሉ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሉሰው ዘውዴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በመንግሥትና በሕዝብ ተቋማት ውስጥ የሚፈፀሙ ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ ነው።

ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመከላከል ረገድ የሕብረተሰቡ ግንዛቤና ትብብር እያደገ መምጣቱንም ገልጸዋል።

ለአብነትም በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት 659 ጥቆማ ከሕብረተሰቡ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሠረት ለ171 ጥቆማዎች አስቸኳይ የመከላከል ሥራ እና ለ138 ጥቆማዎች አሥተዳደራዊ ርምጃ በመውሰድ መፍትሔ መሰጠቱን አረጋግጠዋል።

በአስቸኳይ ሙስና መከላከልና በኦዲት ግኝት ከ47 ሚሊየን 560 ሺህ ብር በላይ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ከምዝበራ ማዳን መቻሉንና ተመዝብሮ የነበረም በኦዲት ግኝት እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ 25 ሚሊየን 444 ሺህ ብር በቅድመ መከላከል ከምዝበራ መዳኑንና ቀሪው በኦዲት ግኝት መመለሱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም 13 ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ እና 166 ሔክታር የገጠር መሬት በሙስና ቅድመ መከላከል ሥራ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በሌላ በኩል የ1 ሺህ 281 ሠራተኞችንና 120 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ሀብት በአዲስ የመመዝገብ ሥራ መከናወኑን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም