ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የአዲስ አበባን የስማርት ሲቲ ግንባታ ይበልጥ የሚያፋጥን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የአዲስ አበባን የስማርት ሲቲ ግንባታ ይበልጥ የሚያፋጥን ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የአዲስ አበባን የስማርት ሲቲ ግንባታ ይበልጥ የሚያፋጥን መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ትግበራን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፤ዲጂታል 2030 ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል እድል መፍጠር እንዲሁም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን መገንባት ቁልፍ የስትራቴጂው ግቦች እንደሆኑ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት በመዲናዋ ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት ሥራዎች በስኬት ተከናውነዋል።
በተለይም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በከተማዋ ውጤታማ አፈጻጸም እንደተመዘገበበት ጠቅሰው፤ ይህም ለዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ሽግግር አስተማማኝ መሠረት መጣሉን አስታውቀዋል።
በመዲናዋ በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ የአይሲቲ ፓርክ መጠናከርን ለአብነት አንስተዋል።
ቀደም ሲል በዝቅተኛ ፍጥነትና በወረዳ ደረጃ ተወስኖ የነበረው የኔትወርክ ትስስር መሻሻሉን የገለጹት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት ሰማንያ ስድስት የመንግሥት ተቋማት በሲቲ ኔት (City Net) መሠረተ ልማት መገናኘታቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ተደራሽነት የስትራቴጂው ውጤት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በከተማዋ የመንግሥት አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ በማድረግ ዜጎች ባሉበት ሆነው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የአዲስ አበባን የስማርት ሲቲ ግንባታ ይበልጥ የሚያፋጥንና የዜጎችን ሕይወት የሚያቀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡፡
ስትራቴጂው ዜጎች የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ፣ አዳዲስ የዲጂታል መፍትሔዎችን የሚያመነጩ ፈጣሪዎች እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አመልክተዋል።
በአጠቃላይ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ አዲስ አበባን ዘመናዊና የበለጸገች ስማርት ሲቲ የማድረግ ራዕይን እውን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡