ቀጥታ፡

ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት በጽናት መቆም ይገባል

ወላይታ ሶዶ ፤ ጥር 13/2018(ኢዜአ):- የጀግኖችን ፈለግ በመከተልና ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት በጽናት መቆም አለብን ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ገብረመስቀል ጫላ ገለጹ።

ወላይታን ከ1858 እስከ 1887 ዓ.ም ላስተዳደሩትና የወላይታ የመጨረሻው ንጉስ ለነበሩት ካዎ ጦና የተገነባ የመታሰቢያ ሃውልት ተመርቋል።


 

በምረቃው ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ ገብረመስቀል ጫላ እንደገለጹት የጀግኖችን ፈለግ በመከተልና ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት በጽናት መቆም አለብን።

ካዎ ጦና በንግስና ጊዜያቸው የህዝቦች አንድነትና ሀገር ወዳድነት እንዲጠናከር መስራታቸውን አስታውሰው ታሪኮችን በመጠበቅ አሰባሳቢና የወል ትርክቶችን በመገንባት ለትውልድ የሚሻገር ታሪክ ማስቀመጥ ተችሏል ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድም በተሰማራባቸው መስኮች ሁሉ ሀገሩንና ህዝብን በታማኝነት ማገልገልን ከእርሳቸው ትምህርት መውሰድ አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ እታገኝ ኃይለማሪያም በበኩላቸው፣ የካዎ ጦና የጀግንነትና የልማት ታሪክ ለሀገር ዕድገትና ፍቅር እንዲኖረን የሚያስተምር መሆኑን ገልጸዋል።


 

ንጉስ ጦና ከ131 ዓመታት በኋላ ወላይታን አንድ አድርገው ለመሩበት እና በዓድዋ ድል ጊዜ ዘምተው ላበረከቱት ሀገራዊ አስተዋጽኦ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሐውልት መሠራቱን ተናግረዋል።

የሀውልቱ መቆም በህዝብ ዘንድ አንድነትን በመፍጠር በዞኑና በወላይታ ሶዶ ከተማ የተጀመሩ ልማቶችን ከግብ ለማድረስ መነሳሳትን ይፈጥራል ብለዋል።

የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው ጀግኖችን መዘከርና ታሪክን ማወቅ ያለፈውን በመተንተን ከስህተቶች ለመማርና መልካሙን ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።


 

የህዝቦችን ባህልና ታሪክ ቀጣይነት ለማረጋገጥ ቀደምት ባለውለታዎችን መዘከር እንደሚያስፈልግ ገልጸው፣ በጥንታዊው የወላይታ መንግስት ግንባታ ሂደት ህዝቡ በአንድነት ቆሞ የማይረሳ ታሪክ መስራቱን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ህዝቡ ከመሪዎቹ ጋር በአንድነት በመቆም የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት መትጋት ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም