ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መፍትሄ በመሆኑ ለስኬቱ ድጋፋችንን እናጠናክራለን

ጂንካ፤ ጥር 12/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መፍትሄ በመሆኑ ለስኬታማነቱ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በጂንካ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ ካሉ ባህላዊ እሴቶች መካከል ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርአት አንዱ ሲሆን ይህም ለዘመናዊ የፍትህ ስርአት ጉልህ እስተዋጽኦ ያበረክታል።

በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር እየተካሄደ ባለው ሀገራዊ ምክክር ሂደት ሀገር በቀል የግጭት መፍቻ ዘዴዎችን መጠቀም ያማረ ውጤት እንደሚያስገኝም ነው የሚገለጸው። 

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጂንካ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች እነዚህን ባህላዊ እሴቶች በአግባቡ በመጠቀም ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የሚያደርጉትን ድጋፍና እገዛ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል። 

ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በማሳተፍና ስኬታማ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቶ ወሳኝ የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ የደረሰው ሀገራዊ ምክክሩለሀገር ዘላቂ ሰላም አምጥቶ የማየት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የጂንካ ከተማ የሀገር ሽማግሌ ዳኜ ገብሬ እንዳሉት ሀገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ መፍትሄ ነው።

የቆዩና የማያግባቡ ችግሮች ላይ በጋራ በመምከር ሀገራዊ መግባባት እንዲመጣ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባቱና ሂደቱ ሁሉንም ያሳተፈ መሆኑ የዴሞክራሲ ስርአት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

ሀገር በቀል ችግሮች የሚፈቱት በሀገር በቀል እሴቶች መሆኑን ጠቁመው፣ በኮሚሽኑ የእስካሁኑ ሂደት በአካባቢያቸው ህብረተሰቡን በማስገንዘብና የኮሚሽኑ መድረኮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ለምክክሩ ሂደት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በጂንካ ከተማ የሚገኘው የኔሪ ደብረ ምጥማቅ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መላከ አርያም ቀሲስ ዱባለ ፍሬው በበኩላቸው ሀገር የምትፀናው በምክክር በመሆኑ በማያግባቡ ችግሮች ላይ መወያየትና መፍትሔ ማበጀት መልካም ሀሳብ ነው ብለዋል።

የምክክር ሂደቱ እስከመጨረሻው ስኬታማ እንዲሆን ምዕመኑን ስለሰላምና አብሮነት ከማስተማር በተጨማሪ በምክክሩ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር በማስተባበር ጭምር ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በሀገር ግንባታ የሁሉም ዜጋ ሀሳብና ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በጂንካ ከተማ የሚገኘው የመስጂድ-ሰላም ኢማም ሼህ ኢድሪስ አህመድ ናቸው።

ለትውልዱ የሚበጅ፣ ሀገርን የሚጠቅምና የሚያሳድግ ሀሳብ ያለው ዜጋ ሀሳቡን በማዋጣት ለሀገር ግንባታው የራሱን አሻራ ማኖር  ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ሀገር ሰላሟ ጸንቶ ልማቷ እንዲፋጠን እንደ ሃይማኖት አባት ምዕመናን ሰላምና አንድነታቸውን እንዲያጸኑ የማስተማር ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸው፣ ወደ መገባደድ ደረጃ የደረሰው የምክክር ሂደቱ ስኬታማ ሆኖ የምንፈልገውን ሰላምና ዕድገት እንዲያመጣ ሁላችንም እገዛችንን ማጠናከር አለብን ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውጤታማ የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራዎችን በማከናወን ወደ መጨረሻው የምክክር ምዕራፍ በመድረሱ ለመጨረሻው ስኬት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም